ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ህብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ ችግርን ለመቋቋም ከሚሠሩ አካላት ጋር አብሮ እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

57

መጋቢት 30/2012(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር  አቢይ  አህመድ  ህብረተሰቡ  የኮሮና  ቫይረስ  ችግርን  ለመቋቋም  ከሚሠሩ አካላት ጋር አብሮ እንዲቆም  ጥሪ አቀረቡ።

ከዚህ በተቃራኒ ችግሩን ለማባባስ የሚሠሩ ካሉ ግን፣ በሕጉ መሠረት የማያዳግም ርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ሶስት ስትራቴጂዎችን አውትቶ በመቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

ስትራቴጂዎችም ኅብረተሰቡን አስተባብሮ በባለሞያዎች ምክር መሠረት ለመከላከል መስራት፣ ከመከላከል ያለፈ ነገር ሲመጣ ለማከም  የሚያስችሉ  ዐቅሞችን  ማዳበር  እንዲሁም  የከፋ ነገር ከመጣም አስቀድሞ  በመዘጋጀት  እንደየ  አስፈላጊነቱ  ተገቢ  ውሳኔዎችን እያሳለፉ መሄድ የሚሉት ናቸው ብለዋል፡፡

በዚሁ አጋጣሚ አርሶ አደሮቻችን የበልግ ወቅት እንዳያልፍባቸው ራሳቸውን ከቫይረሱ እየጠበቁ በምርት ሥራ ላይ ጠንክረው እንዲሳተፉ አደራ ብለዋል።

ከቫይረሱ ባልተናነሰ የእርሻ ምርት መቀነስ ብሎም አለመኖር  ሀገራችንንና  ሕዝባችንን  ይጎዳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "እናንተ ሀገር መጋቢዎች ስለሆናችሁ፣ እየተጠነቀቃችሁ ካለፈው የተሻለ ምርት ለማምረት ትጉ፤ መንግሥትም  አስፈላጊውን  ሁሉ   ድጋፍ  ያደርግላችኋል" ብለዋል፡፡

"የኢንዱስትሪ ምርቶቻችንም ፈጽመው መቆም የለባቸውም፡፡ ለሠራተኞቻችን  ሕይወት እየተጠነቀቅን፣ በወረርሽኙ ምክንያት የሚያጋጥመንን ተግዳሮት ሁሉ እየተቋቋምን በፋብሪካ ምርቶች ላይ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ" ሲሉም አክለዋል፡፡

በተለይም ከውጭ የምናመጣቸውን ምርቶች ለመተካት ለሚደረገው ጥረት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ አባላት፣ የፖሊስ ሠራዊት አባላት፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውኃ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል የሚሠሩ ባለሞያዎች፣ የሚዲያ ባለሞያዎች፣ የመገናኛ መሥመሮቻችን ላይ 24 ሰዓት የሚያገለግሉ ዜጎች፣ እኛ ቤት እንድንውል እነርሱ ውጭ የሚውሉ ሠራተኞች ተገቢው ምስጋናና ድጋፍ ከቤተሰባቸውም፣ ከማኅበረሰባቸውም ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም