የ ኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚረዱ ድጋፎች ተደረጉ

69

መቀሌ ፣ሁመራ ፣መጋቢት 30 /2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቐለ ዲስተሪክት ሰራተኞችና ''ራስ አገዝ የሁመራ ልጆች'' ማህበር በክልሉ ለተቋቋመው ኮማንድ ፖስትና ለአቅመ ደካማ ወገኖች የገንዘብና የቁሳቀሱስ ድጋፍ አደረጉ።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቐለ ዲስተሪክት ዳሬክተር አቶ  ኤፍሬም ሰዋሰው   እንደገለጹት   በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላለከል እየተካሄደ ያለውን ጥረት የሚያግዝ ከ2 ሚልዮን 282 ሺህ ብር በላይ  ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉ የዲስትሪክቱ ሰራተኞች ከወርሃዊ ደመወዛቸው በመቀነስ የለገሱት መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በ116 ቅርንጫፎች የሚገኙ ሰራተኞች  እስከ 10 በመቶ ከደመወዛቸው  በመቀነስ በክልሉ ለተቋቋመው ጊዜያዊ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ኮማንድ ፖስት ዛሬ አስረክበዋል።

በተመሳሳይ በሁመራ ከተማ የሚገኝ  ’’ራስ አገዝ የሁመራ ልጆች’’ የተባለ ማህበር ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለአረጋውያንና ለአቅመ ደካሞች የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል።

ማህበሩ ለችግሮኞችና አረጋውያን ከ60 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርና 90 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ አበርክቷል።

የማህበሩ ጸሐፊ መምህር መትከል ግርማይ ለኢዜአ እንደተናገሩት የማህበሩ ዋነኛው ዓላማ የተለያየ ማህበራዊ ችግር ያላቸውና ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ ነው ።

ማህበሩ በሰቲት ሁመራ ከተማ የሚገኙ ለ71 ችግረኛ ወገኖች ለየአንድዳቸው አንድ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ ብርና የንጽህና  መጠበቂያ ሳሙና፣ኦሞ፣አልኮልና ሌሎች ቁሳቁሶችን ሰጥቷል::

የሁመራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዋጋየ በሪሁን እንዳሉት ማህበሩ በዚሁ አስቸጋሪ  ወቅት አቅም ለሌላቸው  ወገኖች መድረሱ ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል ።

ማህበሩ 50 ኪሎ ዱቄት፣ ሽንኩርት ሳሙናና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቀሱስ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ወ/ሮ ዋጋየ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም