የደቡብ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 70 ሚሊዮን ብር በጀት መደበ

87

ሀዋሳ መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ትናንት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ስራ የሚውል 70 ሚሊየን ብር መመደቡን የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ገለፀ ።

በቢሮው የኮሚኒኬሽን ባለሙያ አቶ ተስፋዬ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ምክር ቤቱ በቪዲዮ ኮንፈረንስ  ባካሄደው 111ኛ መደበኛ ስብሰባው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በክልሉ ለሚከናወኑ ተግባራት 70 ሚሊየን ብር በጀት መድቧል።

የክልሉ መንግስት በበሀገሪቱ ኮሮና መከሰቱን ተከትሎ አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ግብረ ሀይል አቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በሽታውን መከላከል እንዲችል የተለያዩ የግንዛቤ ማጎልበቻ ትምህርቶችን ከመስጠት አንስቶ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እስከ ማገድ የሚደርስ ውሳኔዎች በግብረሀይሉ መወሰናቸውን ጠቁመዋል።

ችግሩ ቢከሰት ህሙማንና ተጠርጣሪዎችን ለይቶ ማከሚያና ማቆያ ማዕከላትን ማቋቋም እንደተቻለና ከተለያዩ ባለሀብቶች ፣ ግለሰቦችና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገኙ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በመረከብ ለክልሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች እንዲሰራጩ መደረጉም በጉባኤው ተገልጿል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ከክልሉ መንግስት ጎን በመቆም በገንዘብ፤ በጉልበት፤ በአይነት እና በእውቀት እያደረገ ላለው ድጋፍ መስተዳድር ምክር ቤቱ ምስጋና አቅርቧል፡፡

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ህብረተሰቡ እያካሄደ ያለውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መስተዳድር ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም