የመዳ ወላቡ ዩኒቨርስቲ የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ እየሰራ ነው

102

ጎባ፣ መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዙ ተግባራትን እያከነወነ መሆኑን ገለጸ፡፡

ዩኒቨርሲቲው በስሩ ባለው  የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል አማካይኝነት የጽዳት መጠበቂያ ሳኒታይዘር ማዘጋጀት መጀመሩን አስታውቋል ።

በጎባ ሪፈራል ሆሰፒታል የፋርማሲ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አየለ ማሞ እንደገለጹት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር እያመረቱ ይገኛሉ፡፡

እስከ አሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከ600 ሊትር በላይ ሳኒታይዘር ተዘጋጅቶ በአካባቢው ለሚገኙ የጤና ተቋማትና ለጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ባለሙያዎች መሰራጨቱን አስረድተዋል፡፡ 

ባለሙያው እንዳሉት በርከት ያለ የንጽህና መጠበቂያ በማዘጋጀት አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለማዳረስ ዕቅድ ቢኖራቸውም የመስሪያና ማሸጊያ ዕቃ አቅርቦት ችግር በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ማነቆ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጄይላን ቃሲም በበኩላቸው ሆስፒታሉ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከኮሮና በሽታ ተጋጭነት ለመከላከል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ህሙማን ስለ ወረርሽኙ ምንነትና መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ የግንዛቤ ትምህርት እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ጄይላን እንዳሉት የማህበረሰቡን የበሽታ ተጋላጭነት ለመቀነስ ማንኛውም ወደ ሆስፒታሉ የሚገባ ሰው በር ላይ የሰውነት ሙቀቱ እንዲለካ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር ለታ በከሬ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡን ከኮሮና ተጋላጭነት ለመከላከል ግንዛቤ በማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡

በዞኑ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ በተገመቱ የባሌና ምዕራብ አርሲ ዞኖች የገጠር ወረዳዎች ውስጥ ዘላቂ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ላይ ነን ብለዋል። 

ዶክተር ለታ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የግንዛቤ ተግባራትን ከማከናወን በተጓዳኝ ሳኒታይዘር የማዘጋጀትና ከ250 የሚበልጡ ክፍሎችን ለለይቶ ማቆያ ማዕከልነት የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ።የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በተለያዩ ፕሮግራሞች በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዶክተር ለታ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም