ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማህበራዊ ትረስት ፈንድ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገለት

106

መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገለት።

የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፉን ያደረጉት የተለያዩ የእምነት ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ናቸው፡፡

ለትረስት ፈንዱ የተደረገው ድጋፍ 6 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ሲሆን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ መሆኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ የአስተዳደሩን ጥሪ በመቀበል ድጋፍ ላደረጉ የእምነት ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ወይዘሮ ዓለምፀሐይ በዚሁ እንዳሉት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ማስቆም የሚቻለው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ራሱንና ቤተሰቡን ለመጠበቅ ተገቢ ጥንቃቄ ሲያደርግ ነው።

ወረርሽኙን ለማስቆም ከሚደረገው የቅድመ መከላከል ድጋፍ በተጨማሪ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ማገዘ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

"በየአካባቢው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እያደረገ ያለውን ድጋፍ በማጠናከር የቫይረሱን የስርጭት መጠን በጋራ መከላከል ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ሳምሶን በቀለ መሰል ድጋፍ ማድረግ አንዱና ዋናው የድርጅቱ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ኢማሞች ማህበር ፕሬዚዳንት ሸህ መሃመድ ጦይብ በበኩላቸው የኮሮናቫይረስን ለማጥፋት የሚደረገው ርብርብ ወደ ፊትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

ህዝቡ በመንግስትና በጤና ባለሙያዎች ብሎም በእምነት አባቶች የሚሰጡ መመሪዎችን ተግባራዊ በማድረግ የኮሮናቫይረስን በጋራ መዋጋት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የክርስቶስ አምባሳደሮች ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያንን የወከሉት ፓስተር ሚሊዮን አማኑኤል በበኩላቸው 100 ሺህ ብርና ባለሰባት ወለል ሕንጻ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በመንግስት እየተደረጋ ላለው ጥረት እንዲውል ቤተክርስቲያኗ ድጋፍ ማድረጓን ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ አጋርነታቸውን ለማሳየት እና ሌሎችን ለማነሳሳት ሲባል የተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም