የኢጋድ ሰራተኞች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ለኢትዮጵያ ያደረጉትን የ100 ሺህ ዶላር ድጋፍ አስረከቡ

98

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ሰራተኞች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ለኢትዮጵያ ያደረጉትን የ100 ሺህ ዶላር ድጋፍ ለብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ-ሃይል ኮሚቴ አስረከቡ።

ሰራተኞቹ ለሰባቱም የኢጋድ አባል አገሮች ተመሳሳይ ድጋፍ በማድረግ በአጠቃላይ 700 ሺህ ዶላር ድጋፍ አድርገዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገኝተው በኢትዮጵያ ለተቋቋመው ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የድጋፍ ገንዘቡ ባንክ ገቢ የተደረገበትን ደረሰኝ ያስረከቡት የሰራተኞች ተወካዮች እንደገለጹት፤ ችግሩን ለመከላከል ተቀናጅቶ መስራት ያስፈልጋል።

ሰራተኞቹ ለአባል አገሮች ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በሰራተኞቹ የተደረገው የ100 ሺህ ዶላር በወቅቱ ምንዛሬ ተመን መሰረት 3 ሚሊዮን 291 ሺህ 360 ብር ጂቡቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ መደረጉም ተገልጿል።

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከኢዜአ ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ድጋፉ የኢጋድ ሰራተኞች ለአባል አገሮች ያላቸው የአብሮነት ማሳያ ነው።

''የገንዘቡ መብዛትና ማነስ ሳይሆን በዚህ ክፉ ጊዜ መተባበር አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ሲባል የተደረገ ነው'' ብለዋል።

የኮሮናቫይረስ በቀጣናው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ኢጋድ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ወርቅነህ፤ በተለይም በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ወረርሽኙ እንዳይከሰት ቅድመ ጥንቃቄ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት የቀጣናውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት የመከላከል ጥረት ለማገዝ የ60 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዋና ጸሐፊው፤ ኢጋድ የሚደረጉ ድጋፎችን የማስተባበርና የማሰባሰብ ተግባር እንደሚያከናውንም አመልክተዋል።

በተጨማሪም በአባል አገሮች ድንበር አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦችን ከችግሩ ለመጠበቅ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ-ሃይል ኮሚቴን በመወከል ድጋፉን የተረከቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ኢጋድ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ችግሩን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ አካላት በጥሬ ገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም