በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የምግብ እጥረት እንዳይይከሰት እየተሰራ ነው

69

መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) በኮረኖቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የምግብ እጥረት እንዳይከሰት የሚያስችሉ ስራዎችን ለይቶ እየሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የምርት መጠንና አይነት መጨመር፣ በግብዓት አቅርቦትና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ ድጋፍ የማድረግ ተግባራት ይከናወናሉ ብሏል። 

የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በሰጡት መግለጫ በአገር አቀፍ ደረጃ የተዋቀረው ግብረሃይል ከሚተገብራቸው ስራዎቹ ጎን ለጎን በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ቀውስ እንዳይፈጠር የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መጀመሩን ገልጸዋል።

20 በመቶው ህዝቧ ከድህነት ወለል በታች የሚገኝባት ኢትዮጵያ ከበርሃ አንበጣ በተጨማሪ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የምግብ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ስጋት መኖሩን ጠቅሰዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአርሶ አደሩ ግብዓት ግዥና አቅርቦት፣ በኤክስፖርት፣ ልማታዊ ሴፍትኔት በታቀፉ ዜጎችና በምርትና ምርታማነት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

በአገር ውስጥ የሚከሰተውን የምርት ክፍተት ለመሙላት መንግስት ከውጭ በሚያስገባቸው የምግብ ምርቶችና ለአርሶ አደሩ ግብዓት ግዥዎችም ላይ መስተጓጎል ይፈጠራል ብለዋል።

በልማታዊ ሴፍትኔት በታቀፉ ዜጎች ላይ ወደ 8 ሚሊየን ከሚጠጉ ዜጎች በተጫማሪ ሌሎች ወደ ተረጂነት የሚሸጋገሩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ለችግሩ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ለችግሩ መፍትሄ ለመሻት መንግስት የረጂምና የአጭር ጊዜ ዕቅዶችን ለይቶ ወደ ስራ መገባቱን፤ በተለይም በቀጣይ ስድስት ወራት በሚተገበሩ ስራዎችን ታሳቢ ተድርጎ እንደሚሰራ ሚንስትሩ ገልጸዋል።

በምግብ ምርትን በአይነትና በመጠን ለመጨመር በመስኖ ስራዎች፣ የበልግና የመኸር ስራን በማጠናከር በሰብል ምርትና አትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦትን ማሳድግ አንዱ እርምጃ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል እስካሁን ለአርሶ አደሩ የማዳበሪያ፣ ኬሚካልና ሌሎች የሜካናይዜሽን ግብዓቶችን በፍጥነት ማዳረስ ሲሆን እስካሁንም 70 በመቶ ግብዓት መከፋፈሉን ገልጸው፤ አርሶ አደሩ ከወዲሁ እንዲወስድ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በቀጥታም ሆነ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን በልማት ሴፍትኔት ሲረዱ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስራዎች ቢቆሙም እርዳታውን የማስቀጠል፣ አርሶ አደሩ ከጋርዮሽ አመራርት ወደ ቤተሰባዊ ስራዎች እንዲገባ ማድርገም ሌላው እርምጃ መሆኑ ጠቅሰዋል።

በዚህም ከክልሎች ጋር ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።

በአበባና በሌሎች የውጭ ምርቶች ላይ ለሚደርሰው ጉዳትም ከመንግስት ድጋፍ የሚያገኙበት እድል እንዲመቻች የማድረግ ስራ ገቢራዊ ይሆናል ብለዋል።

በአጠቃላይ የጉዳት ግመታውን ከመግለፅ ቢቆጠቡም በምርትና ምርታማነት ላይ ወረርሽኙ ከፍተኛ ጉዳት  በማስከትል ርሃብ ሊያስከትል ስለሚችል ህብረተሰቡ በሽታውን ከመከላከል ጎን ለጎን የግብርና ስራውን አጣጥሞ መተግበር እንዳለበት አሳስበዋል።

በተለይም የሰብል አመራረት ስርዓቱን ከጋርዮሽ ወደ ቤተሰባዊ እንዲያደርግ፣ የግብይት ሰንሰለቱንም በህብረት ስራ ማህበራት በኩል እንዲከውን እንዲሁም በሰፋፊ የገበያ ሰብል ምርቶች ላይ የተሰማሩትም ባለሃብቶች የፍጆታ ሰብሎችን እንዲያመርቱ ጣልቃ ይገባል ብለዋል።

ይህን ለማድረግም ሀብት መሰባሰብ የሚያስገድድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከመንግስትና ከአጋር ደርጅቶች ሃብት የማሰባሰብ ስራዎች እንደሚደረጉ ተናግረዋል።

ሃብት ከማፈላለግ በተጨማሪም የመረጃ ስርዓቱን በመለወጥ አርሶ አደሩን ግንዛቤ ማስጨበጥና የግብርና ስራዎችን ሳይስተጓጎሉ እንዲከወኑ ይደረጋል ብለዋል።

በዚህም ሚኒስቴሩ ከ69 ሸህ በላይ የግብርና ልማት ጣቢያ ሰራተኞች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ባለሙያዎች በሽታውን ለመከላከል ከጤና ባለሙያዎች ጋር የትብብር ስራቸው ጎን ለጎን በግብርና ስራዎች አርሶ አደሮችን  እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ለባለሙያዎች የሚያስፈልጉ የጤና መጠበቂያ ቁሳቁሶችም እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።

ለዚህም ተማሪዎች ወላጆቻቸውን እንዲያግዙ፣ መገናኛ ብዙሃንም መረጃን በማዳረስና በግንዛቤ ፈጠራው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም