በባህር ዳር ከተማ ቤት ለቤት የፍጆታ ምርቶችን ማቅረብ ተጀመረ

47

ባህር ዳር (ኢዜአ) 29/07/2012 በባህር ዳር ከተማ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ በቤት ውስጥ እንዲቀመጥ በመደረጉ በፍጆታ ምርቶች ላይ የአቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር ቤት ለቤት ማቅረብ መጀመሩን የከተማው ንግድና ገብያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ሙሉዓለም ተፈራ ለኢዜአ እንደገለፁት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሲባል ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ህብረተሰቡ ቤቱ ውስጥ ሆኖ በሽታውን እንዲከላከል ገደብ ተጥሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠርና ህብረተሰቡ ለችግር እንዳይጋለጥ በማሰብ ከመጋቢት 28 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ምርቶችን ቤት ለቤት ማቅረብ ተጀምሯል።

ምርቶቹ እየቀረቡ ያሉት በተመረጡ 11 የህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ሲሆን ቀይ ሽንብኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ጥቅል ጎመን፣ ድንችና መሰል ምርቶች እየቀረቡ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም 350 ኩንታል ቀይ ሽንኩርት ቀርቦ እየተከፋፈለ መሆኑን ጠቅሰው እስከ አሁን ድረስ በጣና እና ህዳር 11 ክፍለ ከተሞች 150 ኩንታል ሽንኩርት ለህብረተሰቡ እንዲደርስ መደረጉን ተናግረዋል።

መንግስት በተመነው መሰረት አንድ ኪሎ ሽንኩርት በ15 ብር ሒሳብ ብቻ እንዲሸጥ እየተደረገ ሲሆን ለጊዜው አንድ ሰው ከአራት ኪሎ በላይ መግዛት እንደማይችልም ጠቁመዋል።

ከማህበራት በተጨማሪም ለስምንት ጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች ሽንኩርት፣ ማካሮኒና ዘይት ቤት ለቤት እንዲያከፋፍሉ ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰው አቅርቦቱም መንግስት ባወጣው ዋጋ እንደሆነ ገልፀዋል።

በቀጣይም ጤፍ ፣ ዱቄትና ፍርኖ ዱቄት ቤት ለቤት እንዲቀርብ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀው  ፍላጎቱ ላላቸው ወፍጮ ቤት ባለቤቶች ፈቃድ በመስጠት አስፈጭተው ከቤት የሚያደርሱበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል ።

ለጊዜው የዘይት አቅርቦት እጥረት መኖሩን የገለፁት አቶ ሙሉዓለም የስኳር ምርት ከዚህ በፊት በተፈጠረው ትስስር መሰረት በበቂ መጠን መቅረብ መጀመሩን ተናግረዋል ።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የንግድ ስርዓቱን አዲስ አሰራር በመዘርጋት እየተሰራ በመሆኑ  ህብረተሰቡ የምርት አቅርቦት እጥረት ይኖራል በሚል አላስፈላጊ መደናገጥ ውስጥ መግባት የለበትም ብለዋል።

በቀጣይም የአቅርቦት ክፍተት እንዳይኖር አቅም ያላቸውን ነጋዴዎችና ባለሃብቶችን በማሳተፍ ሰፊ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ይደረጋል ሲሉ ሃላፊው አብራርተዋል።

መንግስት አቅርቦቱን ለማቃለል ከሚሰራቸው ስራዎች ጎን ለጎንም ለህዝብ የማያስቡ አንዳንድ ነጋዴዎች በግብይቱ ሒደት እጃቸውን እንዳያስገቡ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።

በተለይም የምርት መደበቅ እንዳይኖር ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅስው በትናንትናው እለት በተደረገ ክትትል 26 በርሚል ነዳጅ በድብቅ ሲንቀሳቀስ መያዙን አስረድተዋል ።

የባህር ዳር ከተማ ህብረት ስራ ማህበር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ንግስት አደም በበኩላቸው የህብረተቡን የአቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ምርቶቹን ቀጥታ ከአምራቾች በማስመጣት ለተጠቃሚው እንዲደርስ እየተደረገ ነው።

ህብረተሰቡ ርቀቱን ጠብቆ እንዲገዛ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በዛሬው እለትም ድንች፣ ቲማቲም፡ ሽንኩርትና ቃሪያ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲከፋፈል ተደርጓል ።

በባህር ዳር ከተማ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ ያልተፈለገ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 513 ነጋዴዎች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው እርምጃ መወሰዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም