የህዳሴውን ግድብ ፍሬ ለመቅመስ የተጓዝነው ብዙ፤ የቀረው ትንሽ ነው ... ዶክተር አብርሃም በላይ

108

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2012( ኢዜአ) ''የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ፍሬ ለመቅመስ የተጓዝነው ብዙ፤ የቀረው ትንሽ ነው'' ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቦርድ ሰብሳቢና የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

''ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የብሔራዊ ቁጭታችን እልባት የሚያገኝበት የመጨረሻ ምዕራፍ ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።

የቦርድ ሰብሳቢው ዶክተር አብርሃም ግድቡ የተጀመረበትን ዘጠነኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም የሕዳሴው ግድብ በዚህ ዘመን ላሉ ኢትዮጵያዊያንና ለቀጣዩ ትውልድ የተፈጥሮ ሃብትን ያለምንም ክልከላ በማልማት ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችል ሁነኛ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

"ግድቡ የዘላቂ ልማት መርሃ ግብሮችን ለማሳካት፣ እንደ ትውልድ ደግሞ ሕዝባዊ ቁርጠኝነትን ለማስመስከር የተጀመረ ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው" ብለዋል።

የዛሬ ዘጠኝ ዓመት የተጀመረው ግድቡ በአስተዳደር ቅብብሎሽ የተጠነሰሰ፣ በላቀ ሕዝባዊ ስሜትና ተነሳሽነት ተጀምሮ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ዶክተር አብርሃም አክለውም ''ግድቡ ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ከሚኖረው ፋይዳ ጎን ለጎን ለተፈጥሮ ሚዛን ጥበቃና ለአረንጓዴ ልማት ትልቅ ሚና ያለው ነው'' ብለዋል።

"ግድቡ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሕግጋትና መርሆች ተገዥነቷን፣ መተባበርና መተማመንን የምታስቀድም  እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትና የጋራ መበልጸግ ማሳያ አገር መሆኗን ያሳያል" ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ለዘመናት በወንዙ አጠቃቀም ላይ ሰፍኖ የቆየውን ኢ-ፍትሃዊነት የሚንጸባረቅበትን ሀቅ እንደማትቀበል ሊታወቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

"የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት በሌሎቹ የተፋሰስ አገሮች ዘንድ ምክንያታዊ፣ ፍትሃዊና ጉዳት አልባ የውሃ አጠቃቀምን እንደሚያበረታቱም ይታወቃል" ብለዋል የቦርድ ሰብሳቢው።

ይህ የሚታወቅ ቢሆንም የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና የሰከነ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች ለመፍታት እንቅስቃሴ በመደረጉ የግድቡ ፕሮጀክት ግንባታ መቀጠሉን አመልክተዋል።

በቅርቡ በአሜሪካን መንግስትና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሲካሄድ በቆየው የመግባቢያ ውይይት ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮችን የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ አንድ ሆነው መክተዋል።

"በዚህም በሕግ፣ በርትዕና በፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያልተቃኙ ውይይቶችን እንደማይቀበሉ በማያሻማ መልኩ ለሚመለከታቸው አካላትና ለዓለም ሕዝብ በግልጽ አሳይተዋል፤ ድምጻቸውንም አሰምተዋል" ብለዋል።

ኢትዮጵያም በዓለም ዓቀፍ ሕግ መርሆች መሰረት በቀጣይ ውይይቶች ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኗን የጠቆሙት ዶክተር አብርሃም፤ ''ችግሩን ያስከተለው ፕሮጀክቱ በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ነው'' ይላሉ።

"በቀጣይም የተጓዝነው ብዙ፤ የቀረው ትንሽ መሆኑን በመገንዘብ ግድቡን በማጠናቀቅ ፍሬውን ለመቅመስ ሁላችንም በጋራ መቆሙን መቀጠል ይገባናል" ሲሉ ገልጸዋል።

"በመሆኑንም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ከመከላከል ጎን ለጎን ፕሮጀክቱን በጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርቡ ይቀጥላል" ብለዋል።

በግድቡ ግንባታ ሥራ 24 ሰዓት እየተሳተፉ የሚገኙ ሙያተኞች፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የአካባቢው ነዋሪዎችን አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም