በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች የሶስት ወር ደመወዛቸው ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ተወሰነ

86

መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች የሶስት ወር ደመወዛቸው ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ተወሰነ፡፡

የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ ሙሃመድና የሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተገኙበት እስካሁን የነበረውን አፈፃፀምና በሁለተኛው ዙር አቅጣጫዎች ላይ መክሯል።

የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮጀክቱ ባለፉት አራት አመታት ዜጎችን ከድህነት ለማውጣትና የስራ እድል ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንደነበረው ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ ከአራት አመታት በፊት ከአለም ባንክ በተገኘ 300 ሚሊዮን ዶላርና ከኢትዮጵያ መንግስት 150 ሚሊዮን ዶላር በአጠቃላይ በ450 ሚሊዮን ዶላር በጀት 604 ሺህ ዜጎችን በቀጥታ ድጋፍና የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርጓል።

ስትሪንግ ኮሚቴው በፕሮጀክቱ አፈፃፀምና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመከረ ሲሆን  የፕሮጀክቱን ቀጣይነትና ከኮሮናቫይረስ መከላከል ጋር የተያያዙ ውሳኔዎች በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በኩል ተላልፈዋል።

እስካሁን በ11 ከተሞች ሲተገበር የነበረው ይህ ፕሮጀክት በሁለተኛው ዙር ተጨማሪ 72 ከተሞችን በማቀፍ 826 ሺህ 444 ዜጎችን በቀጥታ ድጋፍና በስራ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በውሳኔው መሰረትም በ11 ከተሞች ሲተገበር የነበረው የመጀመሪያው ዙር የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ዘግይቶ የጀመረ በመሆኑ ለ18 ወራት እንዲራዘም ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው አጠቃላይ 83 ከተሞች ውስጥ ለኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ  16 ከተሞች ተጠንተው ልዩ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚችልም ተወስኗል።

በሴፍቲኔት የታቀፉ ተጠቃሚዎች የኮሮናቫይረስን መከሰት ተከትሎ በመደበኛ ስራቸው ላይ ሳይገኙ የሶስት ወር ደመወዛቸው እንዲከፈላቸውና እየሰሩ ከቆጠቡት ገንዘብ 50 በመቶ ከባንክ አውጥተው እንዲጠቀሙ ተፈቅዷል።

ለሶስት ወራት የሚደረገው ድጋፍ በምግብ ዋስትና ፕሮጀክቱ እንዲታቀፉ የተለዩትን ሁሉንም የድሃ ድሃ ዜጎች ይመለከታልም ተብሏል።

ፕሮጀክቱ እስካሁን ተጠቃሚ ያደረገው 55 በመቶ የሚሆኑትን የድሃ ድሃ ዜጎች ሲሆን ከቀሩት 45 በመቶ ዜጎች ውስጥ 25 በመቶዎቹ በሁለተኛው ዙር ይታቀፋሉ ተብሏል።

ዛሬ የተላለፈው ውሳኔ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከበሽታው ለመከላከል ከተሞች ባወጡት እቅድ መሰረት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ድጋፍ ማድረግንም ይመለከታል።

መንግስት ባለፈው አመት 20 ሺህ የጎዳና ላይ ዜጎችን ለማንሳት ቢንቀሳቀስም አፈፃፀሙ ግን ከ50 በመቶ ያልዘለለ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረው፤ ''ይህ ድጋፍ ዜጎቹ በቫይረሱ ተጠቂ እንዳይሆኑ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያለመ ነው'' ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከፕሮጀክቱ የተረፈና ሌላ አማራጭ በጀት በማፈላለግ 500 ሺህ ዶላር ወጣቶች የተለያዩ ከህሎቶችን አጎልብተው በራሳቸው ስራ እንዲፈጥሩና ተቀጥረው የሚሰሩበት ሁኔታ እንደሚመቻች ገልጸዋል።

ለሁለተኛው ዙር የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት መርሃግብር 738 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን 500 ሚሊዮን ከአለም ባንክ መፈቀዱንና ቀሪው 238 ሚሊዮን ዶላር ከኢትጵያ መንግስት እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም