የኮሮና ቫይረስ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቀንሷል

64

መጋቢት 29/2012 ኢዜአ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ደም የመለገሱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።  

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ እንዳሉት፤መንግስት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መግታት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።

ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎችን መዝጋት፤ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን መገደብ እንዲሁም በርካታ ህዝብ የሚገኙባቸውን ዝግጅቶችን መሰረዝ የመሳሰሉ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውሰዋል።

የተወሰዱ እርምጃዎች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጉልህ ሚና ቢኖራቸውም ደም የሚለግሱ በጎ ፈቃደኞችን ቁጥር ቀንሰውታል ነው ያሉት።

ነገር ግን የካንሰር ህመምተኞች፣ በወሊድ ወቅት ደም የሚያስፈልጋቸው እናቶች እና የድንገተኛ አደጋ የሚገጥማቸው ዜጎች አሁንም ደም ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

በጎ ፈቃደኞች ይህን በመገንዘብ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና ሌሎች ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት የሚወሰዱ ጥንቃቄዎችን በመተግበር ደም የመለገሱን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ አንጻር በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የደም ባንኮች ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት በተለያዩ ክልሎች ባሉ 39 የደም ባንኮች በሳምንት ከአራት ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ደም የሚለግሱ ሲሆን፤ ከቫይረሱ መከሰት በኋላ ቁጥሩ ወደ አንድ ሺህ 300 ገደማ ዝቅ ብሏል።

እስካሁን ባለው መረጃ የኮሮና ቫይረስ ደም በመለገስ እንደማይተላለፍ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የቫይረሱ መኖርና አለመኖር የሚረጋገጠውም ከአፍንጫና ጉሮሮ በሚወሰድ ናሙና መሆኑን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም