የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት ለሚያግዙ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች አንድ ሚሊዮን ዶላር ተዘጋጅቷል

60

መጋቢት 29/2012 ኢዜአ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ የሚፈጥሩ ግለሰቦችን ለማገዝ አንድ ሚሊዮን ዶላር መዘጋጀቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከተባበሩት መንግስታት የልማት መርሃ ግብር (ዩ ኤን ዲፒ) ተወካዮች ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ ውይይት ከተደረገ በኋላ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

በሚኒስቴሩ አስተባባሪነት ዛሬ በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መሰረት የተዘጋጀው ገንዘብ ከሚያዚያ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የፈጠራውን ውድድር ላሸነፉ ግለሰቦች መለቀቅ ይጀምራል ተብሏል።

ከፊርማ ስነ ስርዓቱ በኋላ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሲሳይ ቶላ ለኢዜአ እንደተናገሩት ገንዘቡ የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ሊገታ የሚችል የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤት ላበረከቱ ግለሰቦች የተዘጋጀ ነው።

"ሂደቱ በመንግስት፣ በግልና በአጋር ድርጅቶች የሚሰራውን ሥራ ወደ አንድ ማዕቀፍ በማምጣት በተቀናጀ መልኩ ዘርፉን ለመምራት የታሰበ ነውም" ብለዋል።

በተጨማሪም የፈጠራ ባለሙያዎች አቅማቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማድረግና የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማቅረብ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ተናገርዋል።

ገንዘቡ የጥረት ድግግሞሽን ለማስቅረት እንደሚረዳ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው "እውቀቱ ያለቸው ዜጎች በፍጥነት ጥረቱን ማገዝ እንዲችሉም ዕድል ይፈጥራል" ብለዋል።

የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቱ ኮቪድ-19 ያለበትን ሰው መለየት የሚያስችል፣ በሽታውን መከላከልና ማከም የሚያስችል መሆን እንዳለበት አቶ ሲሳይ ጠቁመዋል።

"ቴክኖሎጂዎቹ ስለበሽታው መረጃ መስጠትና መቀበል የሚያስችሉ ፈጠራዎች፣ የጤና ባለሙያዎች መረጃ የማግኘትና የጤና መረጃ ላይ ያተኮሩ መሆን አለባቸውም" ብለዋል።

የፈጠራ ውጤቱ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሠራተኞች ሥራቸውን ቤት ሆነው የሚሰሩበትን ሁኔታ የሚያቀላጠፍ ከሆነም ይበረታታል ብለዋል።

ገንዘቡ በግልም ሆነ በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በመንግስት የምርምር ተቋማት ውስጥ ያሉ የፈጠራ ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ መሆኑም ታውቋል።

የመጀመሪያ ዙር የገንዘብ ድጋፍ የሚደረገው በሁለት ዙር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ድኤታው፣ ፈጠራው እንደ ተሞከረ አዋጭነቱ ታይቶ 40 በመቶ ገንዘብ የሚለቀቅ ሲሆን ውጤታማ ሲሆን ደግሞ ቀሪው 60 በመቶ ይለቃቃል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የሚያስተባብረው የኮቪድ-19 ተከላካይ የቴክኖሎጂ ኮሚቴ እስካሁን በቫይረሱ ስርጭት ዙሪያ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማበርከቱንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም