ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቀውስ ዙርያ የሚሰራ የምርምር ግብረ ሃይል አቋቋመ

83

ጎንደር፤ 29/07/2012 (ኢዜአ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ በማህበረሰቡ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ በምርምር በመለየት ምክረ ሃሳብ የሚያቀርብ የምርምር ግብረ ሃይል ማቋቋሙን አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ለኢዜአ እንደተናገሩት  የምርምር  ግብረ ሃይሉ ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ትምህርት ክፍሎች  ተውጣጥቶ  የተቋቋመ ነው፡፡

ግብረ ሃይሉ በበሽታው ዙሪያ ጥናትና ምርምር የሚካሄድባቸውን መስኮች በጥናት የመለየት ስራ መጀመሩን  ተናግረዋል፡፡

በጥናቱ ሊካተቱ የሚገባቸውን ጉዳዮች እንዲሁም በዘርፉ ምርምር ላይ የሚሳተፉ ተመራማሪዎችን ለመለየት መስፈርቶችን አውጥቶ ምልመላ ለማካሄድ ግብረ ሃይሉ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለጥናትና ምርምር ስራው በቂ በጀት ከመመደብ ጀምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጀመር ለማድረግ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ውጤቶቹንም ለመንግስት፣ ለባለ ድርሻ አካላትና ለፖሊሲ አውጪዎች ጭምር በማቅረብ ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ እንደሚያመቻችም ገልፀዋል።

የጥናትና ምርምር ውጤቶቹ ማህበረሰቡ በሽታው ከሚያስከትለው ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ቀውሶች ፈጥኖ እንዴት መውጣት እንደንደሚችል በግብአትነት ሊያገለግሉ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሽታውን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድም በአማራ ክልል ከሚገኙ 10 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመረጃና የልምድ ልውውጥ ለማካሄድ የሚያስችለውን የግንኙነት ስርአት ማደራጀቱን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰባዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት አንጻርም ህብረተሰቡ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጥ በተለያዩ ሚዲያዎች በባለሙያዎች ከማስተማር ጀምሮ የሰብአዊ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲው በማራኪ ጊቢ የበሽታው ተጠርጣሪዎች ማቆያ ማእከል መቋቋሙን ጠቁመው በዩኒቨርሲቲው ሆስፒታልም ለታማሚዎች ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ከ300 በላይ አልጋዎች ያሉት ህንጻ ተዘጋጅቷል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በሆስፒታሉ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የላቦራቶሪ መመርመሪያ መሳሪያዎች መደራጀታቸውንና በአዲስ አበባ ስልጠና ወስደው በተመለሱ ባለሙያዎችም የመሳሪያዎች ፍተሻ እየተካሄደ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም