በጉጂ ዞንና በነገሌ ከተማ የኮሮናን ቫይረስ ተጋላጭነት ለመከላከል 150 በጎ ፈቃደኛ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች ተሰማሩ

56

ነገሌ ኢዜአ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓም አርብቶ አደሩ በሚበዛበት በጉጂ ዞን የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ለመከላከል 150 በጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎች ተሰማሩ ። 
ከነገሌ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ከነገሌ ሆስፒታል የተውጣጡ 150 መምህራንና ባለሙያዎች የበጎ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎት ለመስጠት መሰማራታቸውን የከተማው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

የነገሌ ጤና ሳይንስ ኮሌጂ መምህር አበበ ጢቆ ተቀራርቦ መተቃቀፍ ፣ መጨባበጥና መሳሳም በጉጂ ዞን የተለመደ የሰላምታ መለዋወጫ መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ደግሞ አካላዊ ርቀትን ባለመጠበቅ በሰላምታ ልውውጥ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ወቅታዊ የጤና ስጋት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ቫይረሱን ለመከላከል የሰላምታ ልውውጡ ማህበራዊ እርቀቱን የጠበቀ እንዲሆን በበጎ ፈቃደኝነት ማስተማር መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

አላስፈላጊ የሰላምታ ልውውጦችና እንቅስቃሴዎች እንዲገደቡ እሳቸውና ባልደረቦቻቸው ከ5 እስከ 20 ሺህ ህዝብ ለማስተማር ማቀዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሌላዋ የነገሌ ሆስፒታል የጤና ባለሙያ ነርስ የሺ ብርሀኑ በበኩላቸው ሙያዊ እውቀታቸውን በመጠቀም የቫይረሱን ተጋላጭነት ለመከላከል አስተምራለሁ ብለዋል፡፡  

በነገሌ ሆስፒታል ከሚሰጡት የጤና አገልግሎት በተጨማሪ በበጎ ፈቃድ ወቅታዊ የጤና ስጋቱን የመከላከል ሙያዊ ሀላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

ተለላፊ የጤና ስጋቶችን በመከላከል፣በማከምና በማስተማር ከማንም በላይ የጤና ባለሙያዎች የውዴታ ግዴታ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጎ ፈቃደኛ ወጣት ፋጤ አብዱልቃድር በበኩሏ ከመንገስት የሚሰጡ ትምህርቶችና ማስጠንቀቂያዎች እንዲተገበሩ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ከሌሎች 3 ባልደረቦቼ ጋር ለህዝብ እያስተማርን ነው ብላለች፡፡

ቫይረሱን ለመከላከል ውሀ ፣ ሳሙናና አልኮል የመሳሰሉ የንጽህና መስጫዎችን ማቅረብና ተደራሽ ማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካል የሚጠበቅ ስራ እንደሆነም ጠቁማለች፡፡

የከተማው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ገመቹ ነገራ ቫይረሱን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ በራሪ ወረቀቶችና የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያዎች መቅረባቸውን ገልፀዋል ።

የግንዛቤ ትምህርት ለመስጠት 150 በጎ ፈቃደኞች መሰማራታቸውን የገለፁት አቶ ገመቹ ለቫይረሱ መተላለፊያ አመቺ ይሆናሉ ተብለው የተገመቱ የትራንስፖርት ፣ የመዝናኛና አላስፈላጊ የሰላምታ ልውውጦች ላይ ጊዜያዊ ገደብ መጣሉን አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም