የኮሮናቫይረስ ምርመራ በመቀሌ ተጀመረ

91

መጋቢት 29/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ምርመራ በመቀሌ መጀመሩንና ሌሎች ሦስት ቦታዎች ላይ ምርመራውን ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከጀመሩ ሦስት ተቋማት በተጨማሪ በክልሎችም ለማስጀመር እየተሰራ ነው።

አሁን ላይም በአራት ቦታዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው፤ ከእነዚህም መካከል በመቀሌ የምርመራ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ባህርዳር፣ አዳማና ሃሮማያ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ምርመራውን ለመጀመር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ በቅርቡ ምርመራ የሚጀመር መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪ በጂግጂጋ፣ በአርሲ፣ በጅማ፣ በጎንደርና በሐዋሳ ምርመራውን ለመጀመር ሥልጠናዎች ተጠናቀው አስፈላጊውን ቁሳቁስ እየተሟላላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም አዲስ ለሚቋቋሙት የምርመራ ማዕከሎች የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይ ደግሞ በደሴና በአርባምንጭ ምርመራውን ለማስጀመር የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና እንደሚጀመር ተናግረዋል።

እነዚህ ተግባራት በክልሎች አካባቢ የሚደረገው የምርመራ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጠናክረው ጠቁመዋል።

ይህንን ተከትሎም ማንኛውም ኅብረተሰብ የበሽታው ስሜት ካለበት ለጤና ተቋማት በማሳወቅ ምርመራውን በአፋጣኝ እንዲያገኝ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጓዳኝም ኅብረተሰቡ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያደርገውን ጥንቃቄ አሁንም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም