በሐረሪ ክልል መሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ነው

80

ሀረር ኢዜአ መጋቢት 29/ 2012 ዓም በሐረሪ ክልል የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የተጣለውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተከትሎ መሰረታዊ የሸቀጦች እጥረት እንዳይከሰት ለነዋሪው ሀዝብ የተለያዩ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እያከፋፈለ መሆኑን የክልሉ ንግድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ አብራሂም ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከትራንስፖርት እገዳ ጋር በተያያዘ በመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ላይ እጥረት እንዳይከሰት የማረጋጋት ስራ እየተከናወነ ነው ።

በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ 371 ሺህ ሊትር ዘይት በክልሉ በሚገኙ 43 መሰረታዊ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት  በኩል ለነዋሪው፣ ለህጻናት ማሳደጊያና አረጋውያን መርጃ ማዕከል፣ ለመንግስት ሰራተኛና ለሆቴል ቤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መከፋፈሉን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ዱቄት ለዳቦ ቤቶችና ለክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እንዲደርስ ተደርጓል ።

4 ሺህ 500 ኩንታል ስኳር ለነዋሪውና ለንግድ ድርጅቶች እየተከፋፈለ እንደሚገኝ አቶ አብዱል ፈታህ ጠቁመው በአሁኑ ወቅት በክልሉ መሰረታዊ የሸቀጦች እጥረት እንደሌለ ገልጸዋል።

የክልሉ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፈቲያ አብደላ በሰጡት አስተያየት በክልሉ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ባይኖርም በየቀበሌው በሚገኙት  የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት  መሰረታዊ ሸቀጦች በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ እየከፋፈለ ነው ብለዋል ።

ሆኖም እንደ ፓስታና ማኮረኒ ዓይነት  የምግብ ሸቀጦች የሚቀርቡበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

መንግስት ይህንን ወቅት አስቦ ሸቀጦች ለህብረተሰቡ እንዲዳረስ ማድረጉ እጅግ የሚበረታታ ስራ መሆኑን የገለጹት የከተማው ነዋሪ አቶ በለጠ ከተማ በበኩላቸው አቅርቦቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል ።

ባለፈው ሳምንት በስኳር፣ ዘይትና ሌሎች ምግብ ነክ በሆኑ ሸቀጡችና እህል ላይ ዋጋ በጨመሩ 25 ነጋዴዎች ከ2 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር እንዲቀጡ ተደርጓል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም