የሰቲት ምርምር ማእከል የበግ ዝርያዎችን ለማሻሻል እየሰራ ነው

84

ሰቲት ሁመራ መጋቢት 28/2012(ኢዜአ) የሰቲት ሁመራ ግብርና ምርምር ማእከል በአንድ ጊዜ እስከ አራት ግልግሎች የመውለድ አቅም ያላቸውን የበግ ዝርያዎች ከአካባቢው ዝርያዎች ጋር የማዳቀል ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

ባርካና ረጢባ የተባሉ የበግ ዝርያዎች በአራት ወራት ውስጥ ከ45 ኪሎ በላይ እንደሚመዘኑ ተገልጸዋል።

በማዕከሉ የእንስሳት ምርምር የበግ ዝርያ ማሻሻያ ተመራማሪ አቶ ሽሻይ ማርቆስ ለኢዜአ እንደገለጹት  በቃፍታ ሁመራ ወረዳ በረከት፣ሴንትራል፣ራውያን እና ማይ ካድራ በተባሉ  ቀበሌዎች የሚገኙ የበግ ዝርያዎችን የማሻሻል ስራ ጀምሯል ።

ማእከሉ በአንድ ጊዜ እስከ አራት ግልገሎችን ለመውለድ የሚችሉ በጎች ለሃያ አንድ አርሶ ማከፋፈሉን ገልጸዋል።

ዝርያዎቹ በአራት ወራት ውስጥ እስከ 45 ኪሎ የሚመዘኑ በመሆናቸው ወደ ውጭ ስጋ በሚልኩ ነጋዴዎች ዘንድ ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ተመራማሪው ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚታወቁ በጎች ግን በአራት ወራት ውስጥ ከ25 ኪሎ ግራም እንደማይበልጡ አስረድተዋል ።

በዞኑ ውስጥ ከሰባት በላይ የበግ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ማእከሉ በጋይትና ሩጣባ በተባሉ ዝርያዎች ላይ ትኩረት በመስጠት የማሻሻያ ምርምር እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርምር ማእከሉ የነበረች አንዲት የበጋይት ዝርያ ያላት በግ ባለፈው ሰኔ ወር  ላይ በአንድ ጊዜ ስድስት ግልገሎችን መውለድዋን ጠቅሰው የዝርያዎቹ ተፈላጊነት በአብነት በማስደገፍ  ተመራማሪው ተናግረዋል።

ማእከሉ ዝርያዎቹን በሚቀጥለው ሰኔ ወር ወደ ተጨማሪ  አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ 1ነጥብ6 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ እየሰራ ይገኛል ብለዋል ።

የሰቲት ሁመራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መልካም ታደሰ በሰጡት አስተያየት የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው አስር እናት በጎችን እያራቡ መሆናቸውን ገልፀው አንዲት የበጋይት ዝርያ እንስት በግ እስከ 5 ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዓመት ሁለት ጊዜ ከሶስት  መንታዎችን በላይ ስለሚወልዱ ዝርያዎቹ ተፈላጊ ናቸው ያሉት ደግሞ የሰቲት ሁመራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ግደይ ሕሉፍ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም