በጋምቤላ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተላለፉ ውሳኔዎችን የጣሱ 150 ተሽከርካሪዎች ተያዙ

74

ጋምቤላ ኢዜአ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓም የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ያሰተላለፋቸውን ውሳኔዎች ጥሰው የተገኙ 150 ተሽከርካሪዎች መያዙን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ ። 

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡቲያንግ ኡቻን ለኢዜአ እንደገለጹት 150 የሞተርና የባጃጅ ተሽከርካሪዎች በቀጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት አሽከርሪዎቹ የክልሉ መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል ለ14 ቀናት ያስተላፋቸውን ውሳኔዎች ተላልፈው በመገኘታቸው ነው።

ቫይረሱን ለመከላከል የባጃጅ ትራንሰፖርት ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም የሞተር ሳይክሎች ደግሞ ከአንድ በላይ እንዳይጭኑ መንግስት ውሳኔ ቢያሳልፍም አሽከርካሪዎች ውሳኔዎችን ተላልፈው በመገኘታቸው ተሽከርካሪዎቻቸው እንዲያዙ ተደርጓል ።

ባለፉት ሁለት ቀናት በኮሚሽኑ ክትትል በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተሽከርካሪዎች መካከል 137ቱ ሞተሮች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ባጃጆች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ደንብ የተላለፉትን አሽከርካሪዎች ከገንዘብ ቅጣት ባለፈ በቀጣይ መሰል ችግሮችን አንፈጥርም ብለው ካልፈረሙ በስተቀር ተሽከርካሪዎቻቸው እንደማይለቀቁ ተግናረዋል።

በቀጣይም የክልሉ መንግስት ለ14 ቀናት እንዲተገበሩ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች በማይፈጽሙ አካላት ላይ ኮሚሽኑ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

በመሆኑም በመንግስት ለተላለፉት ውሳኔዎች ተግባራዊነት ሁሉም የክልሉ ህዝብ የበኩሉን እንዲወጣ ኮሚሽነር ኡቱያንግ  ጥሪ አቅርበዋል ።

በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከመጋቢት 23 ቀን 2012 ጀምሮ ለ14 ቀናት ተግባራዊ የሚደረጉ ውሳኔዎች መተላለፋቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምእመናን በመንግስት የሚተላለፉ መመሪያዎችን በመተግበር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ፆምና ፀሎታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የጋምቤላ፣ቤሻንጉል፣ ምዕራብ ወለጋና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል አሳስበዋል ።  

ሊቀ ጳጳሱ ባስተላለፉት መልእክት ምዕመናኑ በመንግስት የሚተላለፉ መረጃዎችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ፈጣሪ ከቫይረሱ እንዲጠብቃቸው ፆምና ፀሎታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የኮሮና ወረርሽኙን ለመከለካል በሚደረገው ጥረትም ቤተ ክርስቲያኗ ከመንግስት ጎን በመሆን የተቻላትን ሁሉ አስተዋፅኦ ለማበረከት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳሱ በጋምቤላ ከተማ በመዘዋወር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ስርዓተ ማህጠንት አካሄደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም