የኢትዮጵያ ዉሹ ሻምፒዮና በአዳማ ተጀመረ

135
አዲስ አበባ ሰኔ 25/2010 የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዉሹ ሻምፒዮና በአዳማ ከተማ የቀድሞ ምክር ቤት አዳራሽ ተጀምሯል። ከማርሻል አርት ስፖርቶች አንዱ በሆነው የዉሹ ስፖርት ሻምፒዮና ላይ ከሰባት ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 273 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉሉ። የኢትዮጵያ ዉሹ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳኜ ለኢዜአ እንደገለጹት ስፖርተኞች ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከርና በስነ-ምግባር የታነጹ ስፖርተኞችን ማፍራት የውድድሩ ዓላማ ነው። ሻምፒዮናው ተወዳዳሪዎች የስልጠና ውጤታቸውን በውድድሩ የሚለኩበትንና የሚመዝኑበትን መድረክ  እንደሚፈጥር ገልጸዋል። የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በተለያዩ ምክንያቶች በሻምፒዮናው ላይ እንደማይሳተፉ ለፌዴሬሽኑ ማሳወቃቸውን አመልክተዋል። ትናንት ተሳታፊ ክልሎች የቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ያደረጉ ሲሆን የሻምፒዮናው ውድድሮች ዛሬ መካሄድ እንደሚጀምሩም ጠቅሰዋል። ሻምፒዮናው በዉሹ አርት ( በመሳሪያ እና ያለመሳሪያ ) እንዲሁም በነጻ ፍልሚያ (ከ48 እስከ 70 ኪሎ ግራም ዘርፍ) ተከፍሎ በሁለቱም ጾታዎች እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። የሶማሌ ክልል በሁለቱም ጾታዎች በዉሹ አርት የሚሳተፍ ሲሆን ቀሪዎቹ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሁለቱም ጾታዎች በዉሹ አርትና በነጻ ፍልሚያ እንደሚሳተፉ ነው አቶ ዳንኤል ያስረዱት። በዚህም መሰረት ዛሬ በወንዶች ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም የነጻ ፍልሚያ ውድድር እንዲሁም በዉሹ አርት በሁለቱም ጾታዎች ውድድር እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ዉሹ ሻምፒዮና እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም