የፒያሳ አትክልት ተራ ወደጃን ሜዳ ዛሬ ይዛወራል ቢባልም የመገበያያ ሥፍራው ለአገልግሎት ክፍት አልሆነም

155

አዲስ አበባ፣መጋቢት 28/2012 (ኢዜአ) ከፒያሳ አትክልት ተራ ከዛሬ ጀምሮ ወደጃን ሜዳ ይዘዋወራል የተባለው የመገበያያ ሥፍራ በመሰረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት በዛሬው እለት ለአገልግሎት ዝግጁ አለመሆኑ ተገለፀ።

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር እና የህዝብ ግንኙነት ተወካይ አቶ ዳንኤል ሚኤሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የፒያሳው አትክልት ተራ የገበያ ሥፍራ ከዛሬ ጀምሮ ወደጃንሜዳ እንዲዛወር ተወስኖ ነበር ።

ይሁንና በነጋዴዎች ተጨማሪ ጥያቄ መሰረት የእነሱን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል ያልተሟሉ የግማሽ ቀን ሥራዎችን ለማከናወን እንዲቻል በዛሬው ዕለት በስፍራው የገበያ አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩን ተናግረዋል።

በጃንሜዳ የተዘጋጀው የገበያ ስፍራ ለመኪና መግቢያ እና መውጫ አመቺ እንዲሆን ነጋዴዎች በመጠየቃቸው ምክንያት ያን ለማስተካከል ሲባል ስፍራው ዛሬ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዳልተደረገ ገልጸዋል።  

አቶ ዳንኤል እንዳሉት፤ የገበያ ስፍራው ከፒያሳ ወደጃንሜዳ እንዲዛወር የተደረገው የሰዎችን የጥግግት መጠን በመቀነስ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ታስቦ ነው።

መተላለፊያ መንገድ እንዲዘጋጅ መደረጉ ለተሽከርካሪዎች፣ ለእቃ አውራጅና ጫኞች እንዲሁም ለሸማቾች ይበልጥ አመቺ መሆኑን አስረድተዋል።

በቦታው የገበያ አገልግሎት ዛሬ ባይጀመርም በአንድ ቀን መዘግየቱ ለህዝብ ጥቅም ሲባል እንደሆነ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል።

በፒያሳ የሚገኘው የአትክልት ተራ የመገበያያ ሥፍራ በዛሬው ዕለትም መደበኛ የግብይት ሥራ እየተከናወነበት ስለመሆኑ ኢዜአ ማረጋገጥ ችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም