ከብዙሃን ትራንስፖርት በስተቀር ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት ከጥዋቱ 12 እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ ብቻ እንዲሰሩ ተወሰነ

206

አዲስ አበባ ፣መጋቢት 28/22012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ተከትሎ ከብዙሃን ትራንስፖርት በስተቀር ከነገ ጀምሮ ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት ከ12 እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ ብቻ እንዲሰራ መወሰኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖት ቢሮ አስታወቀ።

ይህን ውሳኔ በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ  ከ5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እስከ እስራት የሚደርስ  እንደሚደረግ አስጠንቅቋል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ስጦታው አካለ አዲስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መዛመት ለመከላከል ሲባል በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የተላለፉ አዳዲስ ውሳኔዎችን ይፋ አድረገዋል።

ውሳኔውም አንበሳ፣ ሸገር፣ ሃይገር፣ አነስተኛና መካከለኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን ጨምሮ ታክሲ፣ ባጃጅና ሞተርሳይክሎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።

በዚህም መሰረት የብዙሃን ትራንስፖርት ማለትም ሸገርና አንበሳ አውቶቡሶች ቀድሞ እንዲጭኑ ይፈቀድላቸው ከነበረው ከ70 አስከ 90 ተሳፋሪ የመጫን አቅማቸውን ወደ 30 ሰው ዝቅ እንዲያደርጉ ተወስኗል።

በአዲሱ ውሳኔ የዋጋ ታሪፍ ደግሞ በብዙሃን ትራንስፖርት በኩል የዋጋ ለውጥ አይደረግም።ታክሲ፣ ሀይገር ባስ፣ መለስተኛና አነስተኛ ህዝብ ማመላለሻዎች ደግሞ በወንበር ከመጫን አቅማቸው በ50 በመቶ እንዲቀንሱና ቀድሞ ከነበረው ታሪፍ በእጥፍ ተሳፋሪዎች እንዲከፍሉ ውሳኔ መተላለፉን ይፋ አድርገዋል።

ባለሁለት እግር ወይም ሞተርሳይክል ከአሽከርካሪው ውጭ ሌላ ተጨማሪ ሰው መደረብ የተከለከለ ሲሆን ባለሶስት እግር ተሽሽከርካሪ ወይም ባጃጅ ደግሞ አሽከርካሪው አንድ ሰው ብቻ እንዲያሳፈር ተወስኗል።

 ከዋጋ በተጨማሪ በህዝብ ተሽከርካሪዎች ላይ የስራ ሰዓት ማስተተካከያ ተደርጓል።

በዚህም መሰረት ከብዙሃን ተሽከርካሪዎች (ከሸገር፣ አንበሳና ፐፕሊክ) በስተቀር የሥራ ሰዓት ከጥዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ብቻ ይሆናል።

''በዚህም ምትክ ሸገር፣ አንበሳና ፐፕሊክ አውቶቡሶች የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ ነው'' ያሉት ሀላፊው።ለውሳኔው ተፈጻሚነት ከመደበኛው የትራፊክ ህግ በተጨማሪ ከፌዴራልና ከከተማ አስተዳደር ፖሊስ የጋራ ግብረሃይል መቋቋሙን ተናግረዋል።

ይህን ህግ የተላለፉ አሽከርካሪዎች ከ5ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት፣ መንጃ ፈቃድ መንጠቅና እስራት የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣል ሃላፊው ገልጸዋል።

ሰዓቱን የመገደብ ውሳኔ የተላለፈው አሽከርካሪዎች ከቁጥጥር ሰዓት ውጭ ተሳፋሪዎችን ሲያስተናግዱ በመደራረብ ለቫይረሱ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠሩ በማለም እንደሆነ አመልክተዋል።

የዋጋ ጭማሪው የከተማዋን ነዋሪ ለጫና መዳረጉ ለምን አስፈለገ ለሚለው በሰጡት ምላሽ ቢሮው ህብረተሰቡ ከቤት መዋልና በእግሩ መንቀሳቀስ እንደ አማራጭ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

ባቡርን ጨምሮ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችም ለከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደአማራጭ አገልግሎት እንደሚሰጡም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም