የዋግ ህምራ ብሔረሰብ ዞን 20 የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪዎች በድጋፍ አገኘ

64

ሰቆጣ ፣ መጋቢት 28/2012 (ኢዜአ) የዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዙ 20 የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያ በድጋፍ ማግኘቱን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ አሳየ ገብረ ስላሴ ለኢዜአ እንደገለፁት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያዩ የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።

በመከላከል ስራው የሙቀት መለኪያ መሳሪያ ባለመኖሩ የምርመራና የልየታ ስራውን ለማከናወን እንቅፋት ሆኖ መቆቱን ገልፀዋል።

በድጋፍ የተገኙት የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎችንም በብሄረሰብ አስተዳደሩ መግቢያና መውጫ መንገዶች፣ በማረሚያ ቤቶች፣ በመናኽሪያና በጤና ተቋማት ቅድሚያ በመስጠት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ይደረጋል።

መሳሪያዎቹን ከሰቆጣ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በድጋፍ የተገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም አስቸጋሪ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የተያዘውን ግብ በተወሰነም ቢሆን ለማገዝ እንደሚጠቅም ገልፀዋል።

የኮሮና በሽታ ዋነኛ የመከላከያ መንገዱ ከአካላዊ ንክኪ መራቅ፣ እጅን ደጋግሞ መታጠብና ሌሎች ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን መተግበር በመሆኑ ህብረተሰቡ በሃላፊነት መንፈስ እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል።

የሰቆጣ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አማረ መሰለ መሳሪያዎቹን ዛሬ ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት የኮሮና መከሰትን ተከትሎ በብሄረሰብ አስተዳደሩ ምንም አይነት የሙቀት መለኪያ መሳሪያ ባለመኖሩ መሳሪያዎቹን ለመግዛት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የንግዱ ማህበረሰብና የከተማው ነዋሪዎች ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ በ80 ሺህ ብር ወጪ የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎችን ገዝተው ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡

ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዙ ቁሳቁሶችንና ሌሎች ግብዓቶችን ለማሟላት ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቱ ከ806 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉንም አቶ አማረ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም