በባህር ዳር ከተማ በቤት ውስጥ የመቀመጥ መመሪያ ሙሉ በሙሉ እየተተገበረ አይደለም

45

ባህርዳር፣መጋቢት 28/2012 (ኢዜአ) በባህር ዳር ከተማ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ቀድሞ ለመከላከል ሲባል በቤት ውስጥ የመቀመጥ መመሪያ ሙሉ በሙሉ እየተተገበረ ባለመሆኑ አሁንም ስጋት ፈጥሮብናል ሲሉ የከተማው ነዋሪዎች ገለፁ።

የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይሉ ያስቀመጠውን በቤት ውስጥ የመቀመጥ መመሪያ በመጣስ የሚስተዋሉ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በፓትሮል  የታገዘ የቅኝት  ስራ  መጀመሩን  የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

በባህር ዳር ከተማ የዳግማዊ ሚኒሊክ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ  አበረ ሙጬ  ለኢዜአ  እንደገለጹት መንግስት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሰውና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዲቆም መወሰኑ አበረታች ተግባር ነው።

ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ በቤት ውስጥ በመቀመጥና ከማንኛውም የጎዳና ላይ እንቅስቃሴ በመገደብ ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው እንዲጠብቅ የወጣውን መመሪያ በመተግበር በኩል ውሱንነት ተስተውሏል።

በቤተ እምነቶች አካባቢና በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ሰዎች በግልና በቡድን ከመጓዝ አለመቆጠባቸው ለበሽታው ስርጭት አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የቫይረሱን ስርጭት መከላከል ውጤታማ ለማድረግ የተቀመጠው ክልከላ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር የሚመለከተው አካል ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ሌላው በከተማው አባይ ማዶ የምድረ ገነት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ደሴ  ምህረቱ  በበኩላቸው  አልፎ አልፎ ሰዎች እገዳውን በመጣስ ከጓደኞቻቸውና  ከቤተሰባቸው  ጋር በመሆን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መመልከታቸውን ገልፀዋል።

ክፍለ ከተሞችና ቀበሌዎች የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶችን በማደራጀት የአካባቢያቸውን ሰው ሙሉ በሙሉ ከቤት እንዳይወጣ መምከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር መሰረት ደባልቄ በበኩላቸው ከኮሮና መከሰት ጋር ተያይዞ የተቀመጡ ክልከላዎች እንዲተገበሩ የፀጥታ መዋቅሩ እተሰራ ነው።

ክልከላዎቹ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበሩም በዋና ዋና መስመሮች እንቅስቃሴን  ማስቆም  መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህነኑ ተሞክሮ በማስፋትም ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች በፓትሮል የታገዘ እንቅስቃሴ ዛሬ ተጀምሯል።

ለፓትሮል የሚያገለግሉ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን በመስጠትም የክልሉ መንግስትና አንዳንድ ባለሃብቶች ያሳዩት ተነሳሽነት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ገብቶ ሰዎችን ለህመምና ስቃይ ከመዳረጉ ባሻገር መግደል መጀመሩን እያየ ህብረተሰቡ ከቤት በመውጣት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት እንደሆነም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያዎችን በመተግበር በህይወት የመኖር ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የጸጥታ ሃይሉ ከሚያከናውነው ተግባር ጎን ለጎንም የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ተሰሚነት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ህብረተሰቡን በማስተማር የጋራ ችግርን በጋራ መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ኮማንድ ፖስት ስጋት ባለባቸው ባህርዳር፣ አዲስ ቅዳም፣ እንጅባራና ቲሊሊ ከተሞች በቤት ውስጥ የመቀመጥ መመሪያ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም