በዓድዋ ከተማ ለ130 የጎዳና ተዳዳሪና ጫኝና አውራጅ ወጣቶች የመጠለያ ድጋፍ ተደረገ

68

አክሱም ፣መጋቢት 28/2012  (ኢዜአ) በዓድዋ ከተማ 130 የጎዳና ተዳዳሪዎችና በመናኽሪያ እቃ በመጫንና በማውረድ ሲተዳደሩ የነበሩ ወጣቶች እራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲካለከሉ የመጠለያና የሳኒታይዘር ድጋፍ ተደረገላቸው።

የከተማው ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ ለኢዜአ እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የክልሉ መንግስት በትራንስፖርት ላይ በጣለው ገደብ መናኽሪያዎች ዝግ ሆነዋል።

የተጣለው ገደብ ተከትሎ በመናኽሪያ እቃ በማውረድና በመጫን ኑሮአቸውን ሲመሩ የነበሩ ወጣቶችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ለችግር መዳረጋቸው ተናግረዋል።

የከተማው አስተዳደሩና ከበጎ አድራጊ ግለሰቦች በመተባበር ለዜጎቹ ጊዝያዊ መጠለያና ከ30 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላው ፍራሽና ሳኒታይዘር ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።

 ሁለት በጎ አድራጊ የከተማ ነዋሪዎች ደግሞ  28 ሺህ ብር ዋጋ ያለው  የፍራሽና አንሶላ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ጠቅሰዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ባለሃብቶችን በማነጋገር ወጣቶቹ ምግብ በነጻ የሚያገኙበት ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ድጋፍ ካደረጉ ባለሀብቶች መካከል  ወጣት ሮቤል ፍስሃ እንዳለው ዜጎች በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ  ባለሀብቶች የዜግነት ግዴታ የመወጣት ሀላፊነት አለባቸው  ብሏል።

የመናኽሪያ ስራ ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ በትራንስፖርት ላይ ገደብ ሲጣልበት ኑሮአችን አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል ያለው ደግሞ ወጣት ኤፍሬም ባህታ ነው።

አሁን የከተማ አስተዳደሩና በጎ አድራጊ ግለሰቦች ባደረጉላቸው ድጋፍ ጊዚያዊ መጠለያና ምግብ በነጻ ማግኘታቸውን ገልጿል።

በተመሳሳይ በሽረ እንዳስላሴ መናኽሪያ በእቃ ጫኝና አውራጅ የሚሰሩ 83 ወጣቶች በከተማው የሚገኙ ባለ ሀብቶች ለአስር ቀናት የቁርስ፣ምሳና እራት ወጪ እንደሸፈኑላቸው ተገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም