የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥ ለኮሮናቫይረስ እንዳያጋልጥ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል

94

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2012 (ኢዜአ) የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥ ለኮሮናቫይረስ እንዳያጋልጥ በጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክትር ሂሩት ካሳው አስገነዘቡ። 
ሚኒስቴሩ ከአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበርና ከሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን የሆቴሎችን አገልግሎት አሰጣት ተመልክቷል።     

በአዲስ አበባ ከካሳንቺስ ጀምሮ እስከ ቦሌ ያሉ ሆቴሎች ድንገተኛ ምልከታ የተደረገባቸው ሲሆን ሆቴሎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ምን ያህል ጥንቃቄ እያደረጉ ነው? የሚለውንም በጉብኝቱ ተዳሷል።  

በጉብኝቱ ወቅት በደንበኛ እጦት ምክንያት አገልግሎት ያቆሙ፣ ባር ያላቸው ሆቴሎች ባራቸውን መዝጋታቸው በነበረው ምልከታ ተረጋግጧል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደተናገሩት፤ አብዛኞቹ ሆቴሎች በጥንቃቄ ረገድ የተሻለ የሚባል ደረጃ ላይ ናቸው።

ሆኖም እንግዶችን አራርቆ በማስቀመጥ በኩል ክፍተት ያለባቸው ሆቴሎች መኖራቸውን ታዝበዋል።

ሆቴሎች የደንበኞች መቀነስን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተስተናጋጆች ርቀታቸውን ጠብቀው አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ይኖባቸዋል ብለዋል።   

ከኮሮና ጋር በተያያዘ በአገሪቷ ያሉ ሁሉም ሆቴሎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

ሆቴሎች የሳኒታይዘርና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እጥረት እንዳይገጥማቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ቀጥታ ግዥ የሚፈጽሙበት ስርዓት ተዘርግቷል።

የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት እንደገለጹት፤ ለእንግዶች አገልግሎት የሚሰጡ ሰራተኞች የውጭና የአገር ውስጥ እንግዶች በብዛት የማግኘት እድል ስላላቸው የአፍ መሸፈኛ ጭምብል፣ ጓንትና የመሳሰሉ መከላከያዎችን ሳይዘናጉ መጠቀም አለባቸው።   

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ቢንያም አስራት እንዳሉትም ሆቴሎች ከገበያው እንዳይወጡ ማህበሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም