የፋብሪካው ባለቤት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

174

አዳማ (ኢዜአ) መጋቢት 27/2012፡- የብራዘርስ ዱቄትና ብስኩት ፋብሪካ ባለቤት በአዳማ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የዳቦ ዱቄት፣ ማካሮኒና አልሚ ምግብ ድጋፍ አደረጉ።

የፋብሪካው  ባለቤት አቶ መሐመድ ሰይድ ኢብራሂም ድጋፉን ባደረጉበት ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የነዋሪዎች እንቅስቃሴ በመገደቡ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖች እገዛ ያስፈልጋቸዋል።

የእነዚህን ወገኖች ችግር ለማቃለል ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 1ሺህ ኩንታል የዳቦ ዱቄትና ማካሮኒ እንዲሁም 4ሺህ ካርቶን ብስኩት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ፋብሪካው ካሉት 4ሺህ 500 ሠራተኞች ውስጥ ግማሽ ያህሉን ከነሙሉ ደመውዛቸው ፍቃድ መስጠታቸውንም አቶ መሐመድ አስረድተዋል።

በእረፍት ላይ ያሉትም ሆነ በሥራ ላይ የሚገኙ የፋብሪካው ሠራተኞች በእንቅስቃሴው መገደብ እንዳይቸገሩ  450 ኩንታል የዳቦ ዱቄት እና 225 ኩንታል ማካሮኒ ድጋፍ ማድረጋቸውንም  አመልክተዋል።

ድርጅቱ መስራት፣ማትረፍና መኖር የሚችለው ህዝብና ሀገር ሲኖር መሆኑን የተናገሩት አቶ ሙሐመድ "ድጋፍ ያደረግነው በሀገራዊ ጥሪ ውስጥ የድርሻችን ለማበርከት ነው " ብለዋል።

በተጨማሪም መንገደኞች በጉዞ ወቅት ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ በፋብሪካው አቅራቢያ በሚገኘው ረቡዕ ገበያ መነኸሪያ  ውስጥ በአንድ ጊዜ ከ20 ሰዎች  በላይ የሚያስታጥብ የውሃ መስመሮች በመዘርጋት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው በበኩላቸው ፋብሪካው ያደረገው ድጋፍ በበሽታው ምክንያት ልደርስ የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከፋብሪካው የተገኘው ድጋፍ በከተማዋ 18 ቀበሌዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ቤት ለቤት የእየተከፋፈለ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከንቲባው እንዳሉት የፋብሪካ ባለቤት  ሠራተኞቻቸው እንዳይቸገሩ ከሚያደርጉት  ድጋፍ በተጨማሪ በሽታውን ለመቋቋም የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ባለሃብቱ ተቀብለው የሰጡት ተግባራዊ ምላሽ ለሌሎች አምራች ድርጅቶች  ምሳሌ የሚሆን ነው።

በእረፍት ላይ ከሚገኙት የድርጅቱ ሠራተኞች መካከል ወጣት አጋር ተስፋዬ በሰጠችው አስተያየት  "ፋብሪካው በበሽታው ምክንያት  ከደመውዝ ጋር እረፍት እንዲንወጣ ከማድረጉም ባለፈ ለእያንዳንዳችን አስር  ኪሎ የዳቦ ዱቄትና አምስት ኪሎ ማካሮኒ ሰጥቶናል" ብላለች።

ለበሽታው እንዳይጋለጡ በማሰብ ከደመውዝ ጋር ፈቃድ እንዲሁም የዳቦ ዱቄትና ማካሮኒ ከፋብሪካው ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው ሰራተኛ  አቶ ለገሰ ለማ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም