የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የአንድ ወር ብሄራዊ ጸሎት አወጀ

98

 አዲስ አበባ መጋቢት 27/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በማስመልከት ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ ብሄራዊ ጸሎት አወጀ።

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ባስተላለፉት መልእክት ከነገ ከመጋቢት 28 ቀን  2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ ፀሎት ታውጇል።

ይህንን የፀሎት አዋጅ ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በቤታቸው ሆነው ለሰው ልጆች ሁሉ የፈጣሪያቸውን ምህረት እንዲለምኑም አባቶች ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህም መሠረት በነገው ዕለት በሶስት የተመረጡ ቦታዎች የጸሎት መርሃ ግብሩ የማስጀመርያ ፕሮግራም የሚከናወን ሲሆን ስነ ስርአቱም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘወትር ምሽት ከ3 እስከ 4 ሰአት ይተላለፋል።

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ዋልታ ቴሌዥን እና በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የሚተላለፍ መሆኑም ታውቋል።

ሁሉም ሰው ወደ ራሱ እንዲመለስና ፀሎትን መረዳዳትን፣ መተዛዘንን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር በማሳየት ከፈጣሪው ጋር ሊታረቅ እንደሚገባም የሃይማኖት አባቶቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሃይማኖት ተቋማቱ ለአንድ ወር የሚያደርጉት የፀሎት ፕሮግራምና አስተምሮት ወጥነት ያለው፣ አንዱ ያንዱን የማይነቅፍ እንደሚሆንም በመግለጫው ተመልክቷል።

በዋናነትም የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ ወደ ፈጣሪ ፀሎት ለማድረግ፣ ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ ለመያዝና ምዕምናን ወደ ራሳቸው ሰላም የሚያተኩሩበት እንደሚሆንም ተጠቅሷል።

በፀሎት ስነ ስርአቱ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያሉ መላ ኢትዮጵያዊያን ባሉበት ሆነው እንዲሳተፉም ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም