በአማራ ክልል ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

56

ባህር ዳር፤  መጋቢት 27/2012(ኢዜአ) በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረሰን ለመከላከል የሚያግዝ በዓይነት የተገኘውን ሳይጨምር ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን በክልሉ የኮሮና መከላከል ድጋፍ አሰባሰብና ክምችት ዘርፍ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የግብረ ኃይሉ  ሰብሳቢ ዶክተር ጥላሁን ማህሪ ለኢዜአ እንደገለፁት ለኮሮና መከላከል የሚውል ጠንካራ የሃብት ማሰባሰብ ስራ እየተካሄደ ነው።

ባለፉት ጥቂት ቀናት በተደረገ እንቅስቃሴም በገንዘብ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቅሰው  በዓይነት ደግሞ 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች በድጋፍ ተገኝቷል።

አምስት ሺህ 200 ኩንታል በላይ የዳቦ ዱቄት ድጋፍና ለለይቶ ማቆያ የሚሆኑ ሆቴሎች በጊዜያዊነት ከባለሃብቶች መገኘቱን ዶክተር ጥላሁን አስረድተዋል።

የባህር ዳር፣ የጎንደር፣ የወሎ፣ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎች ተቋማትም የለይቶ ማቆያ ቦታዎች መመቻቸታቸውንም ጠቁመዋል።

ሀብቱ እየተሰበሰ ያለው ከባለሃብቱ፣ ህብረተሰቡ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት እንደሆነም ተጠቅሷል።

እስካሁን የታየው የሃብት አሰባሰብ የሚያበረታታ እንደሆነ ገልጸው "በቀጣይም በክልሉና በአዲስ አበባ የተቋቋመው ግብረ ኃይል በሃገር ውስጥና በውጭ  ሃብት የማሰባሰቡ ስራ ተጠናከሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

እንደ ዶክተር ጥላሁን ገለጻ   ለቀጣይ ሁለት ወራትም  ለንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አቅርቦት፣ አልባሳት፣ መድኃኒትና ተጓዳኝ  መገልገያዎች  አንድ ቢሊዮን ብር እና ለውሃ አቅርቦት  ደግሞ 300 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል።

ለጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለአረጋውያንና በተለያየ ምክንያት የእለት ምግባቸውን ለማይችሉ ወገኖች አንድ ሚሊዮን 500ሺህ  ኩንታል የምግብ እህል እንደሚያስፈልግም ግብረ ኃይሉ በእቅዱ ለይቶ ወደ ስራ ገብቷል።

ለዚህም  ባለሃብቱ ፣ ተቋማት፣ አርሶ አደሩና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል አቅማቸው በፈቀደ ሁሉ በመለገስ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ሃብት ለማሰባሰብም በየደረጃው ግብር ኃይል ተቋቁሞ በ17 ባንኮች የሂሳብ ደብተር መከፈቱንም አስታውቀዋል።

የኮሮና ቫይረስ ማህበራዊና  ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳያስከትል ጠንካራ ትብብር እንደሚጠይቅ  የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ ተናግረዋል። የክልሉ መንግስት 150 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ቀደም ሲል ዘግበናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም