የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የባህሪ ለውጥ አልመጣም... ጠቅላይ ሚንስትር አብይ

68

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በርካቶች እምብዛም የባህሪ ለውጥ እያሳዩ ባለመሆኑ ስጋታችን ጨምሯል ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ  አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በወቅታዊው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኮሮና ዙሪያ የበርካቶች ቸልተኝነትና የባህሪ ለውጥ አለማሳየት ቫይረሱ እንዳይስፋፋ ስጋት አድሮብናል ብለዋል።

መንግስት በሌሎች አገሮች ያስተዋለውን የዜጎችን እንቅስቃሴ ልገድብ ቢል ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚገጥሙም አስረድተዋል።

በመሆኑም "ሁላችሁም ቤት ግቡ ብንል ቤት የሌላቸው ዜጎች አሉን፤ ቤት ካላቸው ዜጎች መካከል ደግሞ የእለት ጉርሳቸውን ሰርትው የሚገቡ በርካቶች ናቸው" ብለዋል።

መንግስትም ለዜጎች ቤት ለቤት ምግብም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን ለመስጠት ይቸገራል ነው ያሉት።

ትምህርት ቤቶች የተዘጉት በህፃናትና ታዳጊዎች እንዲሁም ወላጆች ዘንድ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ በማሰብ በመሆኑ በያሉበት ሆነው ጥንቃቄ አንዲያደርጉ መክረዋል።

በመሆኑም የቫይረሱን መስፋፋት ለመከላከል መተባበር፣ መተጋገዝና የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ ማድርግ ይገባል ብለዋል።

ወጣቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የኪነ ጥበብ ሰዎችም ለአዳዲስ ፈጠራዎች በመነሳሳት ለህዝባቸው የሚጠቅም አስተዋፆ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው አንድ ቤተሰብ ለሌላ አንድ ቤተሰብ በቀን አንድ ምግብ እንኳን ማካፈል (ማዕድ ማጋራት) የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የኮሮናቫይረስ ከዚህ ቀደም ዓለምን ፈትነው ካለፉ ወረርሽኞች በተለየ መልኩ የሚስፋፋ በመሆኑ በጋራ መከላከልን የሚጠይቅ መሆኑንም አስረድተዋል።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1346 በባክቴሪያ ኢንፌክሺን በዓለም ላይ ተከስቶ የነበረው "ጥቁር ሞት" በአውሮፓ ብቻ 50 ሚሊዮን ህዝብ ፈጅቷል።

በ18ኛው ምእተ አመት ተከስቶ የነበረው ፈንጣጣም ቢሆን ፈታኝ እንደነበር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከመቶ ዓመት በፊት የተከሰተው "ስፓኒሽ ፍሉ" እስከ 100 ሚሊዮን የሚገመት የዓለም ህዝቦችን ገድሏል ብለዋል።

የኮሮናቫይረስም እስካሁን ከ1 ሚሊዮን በላይ የዓለም ህዝቦችን አዳርሷል፤ በርካቶችንም ገድሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዘመን የተሻለ የህክምና አቅምና ዓለምአቀፋዊ ትብብር ቢኖርም የተጠናከረ የጋራ ጥረትን ይጠይቃል ብለዋል።

በተለይ ደግሞ አፍሪካዊያን የቫይረሱን መስፋፋት ለመግታት በጋራ መቆም አለብን ሲሉ መልእክታቸውን አስትላለፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም