የአፍሪካ ልማት ባንክ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል የፆታዊ እኩልነትና የአደጋ ስጋት መጋራት ፈንድ አፀደቀ

130

አዲስ አበባ፣መጋቢት 26/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ልማት ባንክ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል የሚያስችል የፆታዊ እኩልነት እና የአደጋ ስጋት መጋራት ፈንድ አጸደቀ።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ያፀደቀው ፈንድ በአፍሪካ አህጉር ፆታዊ እኩልነትን ለማስፋፋትና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ተገልጿል፡፡

ከለጋሽ አገሮች የሚገኘው ገንዘብም ፆታዊ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ እና ባንኩ በአፍሪካ ለሚገኙ ሴቶች እያደረገ ላለው እገዛ አማራጭ የገንዘብ ምንጭ ይሆናል ተብሏል፡፡

ውሳኔውም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማስፋት ፆታዊ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያበረታታ ተነግሯል፡፡

በባንኩ ታሪክ ስርዓተ-ፆታን በተመለከተ የመጀመሪያና የሚያበረታታ ፈንድ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የፈንዱ የመጀመሪያ ዙር ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት እንዲሆን ተደርጎ ይቋቋማል፡፡

ባንኩ በአፍሪካ የሚገኙ ሴቶች ያለባቸውን ከ42 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ክፍተት ለመደጎም በሚል የነደፈው ዕቅድ አካል ነው።

ውሳኔው የሴቶችን የስራ ዕድል ፈጣሪነት አቅም በመገንባት እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎን ለላቀ የልማት ዕድገት ለመጠቀም ትልቅ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን እንደሚያመላክት ተብራርቷል፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድም የሴቶችን የንድግና ፈጠራ ሥራ ለማበረታታት፣ ከባንክ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል እና የሥራ ዕድል ፈጠራዎችን ለማገዝ የሚያስችል የአደጋ ስጋት ፈንድ አፅድቋል፡፡

በአፍሪካ የፆታዊ እኩልነትን እውን ለማድረግ ያለውን ጥረት ለማገዝ የገንዘብ ፈሰስ ያደረጉት የፈረንሳይ፣ የኔዘርላንድ እና የታላቋ ብሪታኒያ መንግስታት ናቸው ተብሏል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪነውሚ አደሲና “እንደባንክ ይህ ለእኛ ታላቅ ቀን ነው፤ የንግድ ሥራ ባለቤት ለሆኑ የአፍሪካ ሴቶች የገንዘብ ተደራሽነት ችግሮችን በመቅረፍ አዳዲስ መንገዶችን ስለሚሰጥ ቀኑ ለአህጉሪቱም ሆነ ለአፍሪካ ሴቶች ትልቅ  ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ዳይሬክተር ቫኔሳ ማውነጋር በበኩላቸው “ለሴቶች የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ትልቅ ጥረት ነው“ ብለውታል፡፡

የስጋት መጋራት ፈንድ መፅደቁ ደግሞ የሴቶችን ኢኮኖሚ በማበረታታት ተነሳሽነትን እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡

ባንኩም የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የንግድ ስራዎቻቸውንም ለማገዝ 5 ቢሊዮን የሚገመት የአሜሪካን ዶላር የማሰባሰብ ዕቅዱን እንደሚቀጥል ለኢዜአ በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም