በቄለም ወለጋ ዞን ከደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት አንጻር መንግስት የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንዲሰራ የዞኑ ነዋሪዎቾ ጠየቁ

73

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2012(ኢዜአ) በቄለም ወለጋ ዞን ባለፉት ሁለት ዓመታት በዞኑ ሕዝብ ላይ የደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የክልሉ መንግስት የመልሶ ማቋቋም ሥራ መስራት እንዳለበት የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም በቄለም ወለጋ ዞን ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳቶች መድረሳቸውን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

በአካባቢው ታጥቆ በሚንቀሳቀሰው ቡድን የተነሳ የዞኑ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

በቅርብ ጊዜያት እንኳን የሕዝብ መሰረተ ልማት አውታሮች ላይ በዚሁ በታጠቀ ቡድን በደረሰ ውድመት እንደቴሌኮም ያሉ መሰረተ ልማቶች ተቋርጠው እንደነበር ይታወሳል።

መንግስትም በአካባቢው ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የሚሰራው ሥራ ይቀላጠፍ ዘንድ ለሦስት ወራት ገደማ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት አቋርጦ ነበር።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት፤ ከሁሉም በላይ የዞኑ ነዋሪዎች ለሁለት ዓመታት ገደማ የልማት ሥራዎችን በተሳካ መልኩ ማከናወን አልቻሉም።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት የዞኑ ነዋሪዎች መካከል አቶ ፍቃዱ ጋዲሳ በሁለቱ ዓመታት ጊዜ ውስጥ የአካባቢው ሕዝብ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መቆየቱን ገልጸዋል።

"በአካባቢው የዜጎች ሕይወት የተቀጠፈበት፣ እንቅስቃሴዎች የተገደቡበትና ባንኮችም ለዝርፊያ የተዳረጉበት ሁኔታ ስለነበር ችግር ተንሰራፍቷል" ብለዋል።

"ከዚህ ባለፈም በዞኑ በርካታ ልጆች አሳዳጊ አባታቸውን፤ እናቶችም ባሎቻቸውን አጥተዋል" ይላሉ አቶ ፍቃዱ።

አቶ ፍቃዱ አክለውም ችግሩ ለሁለት ዓመታት የቆየ በመሆኑ በየቤቱ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ተናግረዋል።

''ሰው ሁለቱን ዓመታት ሥራውን በአግባቡ ባለመስራቱ ከውጪ ሲታይ ደህና ይመስላል እንጂ የሚበላ እንኳን የለውም'' ይላሉ።

በዚህ ወቅት መንግስት ለተቸገሩ ወገኖች ሊደርስላቸውና አስፈላጊውን ሰብዓዊ እርዳታ በማቅረብ ሊያቋቁማቸው እንደሚገባም ነው የገለጹት።

ሌላው የዞኑ ነዋሪ አቶ ገመዳ ሰንበቶ ችግሩ ከዚህ በላይ የባሰ ጠባሳ ጥሎ እንዳያልፍ መንግስት የጀመረውን ጥረት እንዲቀጥል ይጠይቃሉ።

ሕዝቡም ሰላምና ልማት ይረጋገጥ ዘንድ ከመንግስት ጎኖ ይሆናል የሚል እምነት እንዳለቸውም አቶ ገመዳ ይናገራሉ።

"ወደፊት መንግስት በአካባቢው ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ፋብሪካ ቢተክል ጥሩ ነው" የሚሉት ደግሞ ቀኖ መሳዲ ናቸው።

በዚህ ወቅት ሕዝቡ የሰላምን ጥቅም በአግባቡ ተረድቶ ከመንግስት ጎን እየቆመ መሆኑን ተናግረው ለዘለቄታው የአካባቢው ልማት እንዲጠናከር ጠይቀዋል።


ሰሞኑን በክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በአካባቢው ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም