ለኮሮና መከላከል የሚውል 8 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ተሰበሰበ

61

ጎንደር ፣ባህር ዳር  26/2012 (ኢዜአ) በማእከላዊ ጎንደርና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ለኮሮና በሽታ መከላከል የሚውል 8 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሃብት መሰብሰቡን የየዞኖቹ የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል አባላት ገለፁ።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ ጌታሁን ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት አገልገሎት የሚሆን ሃብት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

እስከ አሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከወረዳ መስተዳድሮች፣ ከአማራ አቀፍ ልማት ማህበርና ከህብረተሰቡ አራት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከአርሶ አደሮችና ነጋዴዎች 147 ኩንታል የምግብ እህል የተሰበሰበ ሲሆን የንግዱ ህብረተሰብና የግል ድርጅቶችም የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርና ሳሙናዎችን ማቅረባቸውን ገልፀዋል።

በዞኑ የሚገኙ በጎ አድራጊ ግለሰቦችም ህንጻዎቻቸውንና ተሸርካሪዎቻችውን ለበሽታው መከላከል ስራ እንዲውል ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡

የዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ደርሶልኝ ፈንቴ በበኩላቸው በበሽታው ሊጠቁ የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አፋጣኝ የህክምና ለመስጠት እንዲቻል በአይከልና በሳንጃ ከተሞች የህክምና መስጫ ማእከላት መቋቋማቸውን ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ ስለ በሽታው በቂ እውቀት ጨብጦ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና በህክምና ሙያተኞች ቤት ለቤትና በመኪና ላይ ቅስቀሳ በማካሔድ የግንዛቤ ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ገንዘብ እየተሰባሰበ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስሜነህ አያሌው ናቸው።

ለበሽታው መከላከል የሚውል ሃብት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከባለሃብቶች፣ ከድርጅቶችና ከህብረተሰቡ እየተሰበሰበ ሲሆን እስከ አሁንም 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል።

በቀጣይም 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የተቋቋመው የገቢ አሰባሳቢ ግብረ ሃይሉ እየሰራ መሆኑን ገልፀው የተሰበሰበው ሃብትም ለአቅመ ደካሞች፣ለአረጋዊያንና ሌሎች ድሃ የህብረተሰብ ክፍሎች ለምግብና ንዕህና መጠበቂያ ይውላል።

ህብርተሰቡን ከማስተማር ጎን ለጎንም በተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ  ክልከላዎች መደረጉን ገልፀዋል ።

በ10 ዋናዋና ከተሞች የአስፓልት መንገዶች ላይ የፀረ-ተህዋስያን መድሃኒት ርጭት ከትላንት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

በቡሬ ከተማ የሚስተዋለውን የውሃ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ጥረት እየደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በፍኖተ ሰላምና በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቡሬ ካምፓስ 2 የለይቶ ማቆያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድሜነህ ልየው ናቸው።  

ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በማጭበርበር ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 111 የንግድ ድርጅቶችና 3 መድኃኒት ቤቶች ላይ የማስጠንቀቂያና የማሸግ እርምጃ ተወስዷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም