በደብረ ብርሃን እገዳ የተላለፉ በገንዘብ ሲቀጡ በጋምቤላ ደግሞ ዋጋ የጨመሩ መደብሮች ታሸጉ

96

ደብረ ብርሀን፣ጋምቤላ ፣መጋቢት 26/ 2012 (ኢዜአ) በደብረ ብርሃን ከተማ የተጣለውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እገዳ ተላልፈው የተገኙ ከ60 በላይ አሽከርካሪዎች በገንዘብ ሲቀጡ በጋምቤላ ደግሞ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ የንግድ መደብሮች ታሽገዋል ።
የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሀላፊው ኮማንደር ታየ ሀብተጊዮርጊስ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሽከርካሪዎቹ ላይ ቅጣቱ የተላለፈው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቋቋመው የዞኑ ግብረ ሀይል ያወጣውን እገዳ ተላለፈው በመገኘታቸው ነው።

አንዳንድ ህገ ወጥ አሽከርካሪዎች  ያልተገባ ጥቅም ለማካበት ሲሉ የተጣለውን እገዳ በመጣስ በከተማ ውስጥና ከከተማ ውጭ ሰዎችን ጭነው እያጓጓዙ መሆናቸውን ፖሊስ በክትትል ደርሶባቸዋል ።

በዚህም 24 መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ 37 ባጃጆችና 17 ጋሪዎች ክልከላውን ጥሰው በማጓጓዝ ላይ እንዳሉ በመያዛቸው ከ1 ሺህ እስከ  2 ሽህ 500 ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

በተጨማሪም መለስተኛ ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው የጭነት በላይ  እስከ 50 ሰዎችንና ባጃጆቹም ከአቅማቸው በላይ  ጭነው ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ እንደነበር ተረጋግጧል።

በበደብረ ብርሃን ከተማ የቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ አስቻለው በቀለ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይሉ በትራንስፖርት ብቻ ሳይሆን በምርቶች ዋጋ ጨምረው በሚሸጡ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይም እርምጃ ሊወስድ ይገባል።

ባለ አምስት ሊትር ዘይት 460 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ጠቁመው ይህም ከሳምንት በፊት ከነበረው እስከ 110 ብር የሚደርስ ጭማሪ በመኖሩ ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል እንዲጎዳ ማድረጋቸውን በማሳያነት  አቅርበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ መቶ አለቃ ጭንቅል ጉቹማ በሰጡት ማብራሪያ ግብረ ሃይሉ በህገ ወጦች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል ።

በሰሜን ሸዋ ዞን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከመጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ መታገዱ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ ዜና በጋምቤላ ክልል ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 121 የንግድ ተቋማት እንዲታሸጉ መደረጉን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቋል ።

የቢሮው ኃላፊ ኮማንደር ኡማን ኡጋላ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት እርምጃው የተወሰደው የኮሮና ቫይረስን በማሳበብ በምግብ፣ በንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ፍጆታዎች ላይ  የዋጋ ጭማሪ አድርገው  በተገኙ ተቋማት ነው።

ከታሸጉት የንግድ ተቋማት መካከል የእህል መጋዝኖች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ሱቆች፣ ሱፐር ማርኬቶችና ሌሎችም እንደሚገኙበት አስታቀዋል።

እርምጃ የተወሰደባቸው የንግድ ተቋማት እንደጥፋተቻው ክብደት ከገንዘብ ቅጣት እስክ ፍቃድ መሰረዝ የሚደረሰ እርምጃ ጭምር እየተወሰደ ነው ተብሏል ።

ቢሮው በተለይም የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ጋር ተያይዞ በምግብም ሆነ በሌሎች የፍጆታ እቃዎች ላይ እጥረት እንዳያጋጥም ግብረ ኃይል አቋቁሞ የክትትልና የቀጥጥር ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም