ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ተብለው ናሙናቸው ከተሰበሰበ 641 ሰዎች 470 ሰዎች ነጻ መሆናቸው ተረጋገጠ

54

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2012( ኢዜአ) ለኮሮና ቫይረሱ ተጋላጭ ተብለው ከአዲስ አበባና ከአዳማ ናሙናቸው ከተሰበሰበ 641 ሰዎች 470 ሰዎች ነጻ መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ቀሪዎቹ 171 ሰዎች ደግሞ ምርመራቸው በሂደት ላይ መሆኑ ተጠቅሷል ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት የምርመራ ሥራውን በማስፋት ከአዲስ አበባና ከአዳማ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ 641 ሰዎች ናሙና ተውስዷል።

እነዚህ ሰዎች በስራ ባህሪያቸው ለቫይረስ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ጠቁመው ነገር ግን በቫይረሱ የተጠረጠሩ አለመሆናቸው አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት ከኢሚግሬሽን፣ ከአየር መንገድ በተለይ የበረራ ሰራተኞች፣ ከጤና ተቋማት ሆቴሎች፣ ከአውብቶብስ ሹፌሮች፣ ከፈጣን ምላሽ ቡድን አባላት፣ ከአስጎብኚዎች፣ ከፋርማሲ ባለሙያዎችና ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ናሙና መወሰዱን ተናግረዋል።  

ይህን ተከትሎም ከአዲስ አበባና ከአዳማ በድምሩ 641 ሰዎች የምርመራ ናሙና የተወሰደ መሆኑን ገልጸው 444ቱ ከአዲስ አበባ 197ቱ ደግሞ ከአዳማ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 314 ከአዲስ አበባ 156 ደግሞ ከአዳማ የተወሰዱት ናሙናዎች ምርመራቸው ተጠናቆ በድምሩ 470 ሰዎች ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

171 ደግሞ ምርመራቸው በሂደት ላይ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም