የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጡ ክልከላዎችን ጥሰው የተገኙ 104 ሰዎች በእስራት ተቀጡ

65

መቀሌ መጋቢት 26 /2012 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል መንግስት የጣላቸውን ክልከላዎች ጥሰው የተገኙ 104 ሰዎች በእስራት መቀጣታቸውን የክልሉ የህግ ማስከበር ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ገለጸ።

በኮማንድ ፖስቱ የፀጥታና ፍትህ ንኡስ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ አማኑኤል አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን ደህንነትና ጤንነት  ለመጠበቅ ሲባል ለቫይረሱ  መስፋፋት ምክንያት ይሆናሉ ብሎ በጠረጣራቸው ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ክልከላ ማድረጉን ገልጸዋል።

መንግስት የጣለባቸውን  ክልከላዎች ጥሰው ከተገኙ 275 ሰዎች መካከል 104 ሰዎች ከ3 ወር እስከ 2 ዓመት  በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን ተናግረዋል።

ቅጣት የተጣለባቸው ሰዎች  ኮማንድ ፖስቱ ያስቀመጣቸው መመሪያዎችን ተላልፈው  ከተፈቀደው በላይ ሰው ጭነው የተገኙ አሽከርካሪዎች  ፣ የታሸጉትን ጫትና መዝናኛ ቤቶች ከፍተው የተገኙና በፍጆታ እቃዎች ላይ ዋጋ የጨመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዋጁን ጥሰው በተገኙ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱ መንግስት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ያለው ቁርጠኝነት ያሳያል  ያሉት ደግሞ የመቀሌ ነዋሪ ሲስተር ሻሼ ሞለቐ ናቸው። 

መንግስት የእኔን የቡና መሸጫ ቤትን ጨምሮ እየወሰደ ያለውን እርምጃ የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ በመሆኑ እንደግፈዋለን ያለችው ደግሞ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወጣት ይርጋለም በላይ ናት።

የፈላ ቡና በመሸጥ በቀን አራት መቶ ብር በማግኘት የምትዳደር ብሆንም ቅድሚያ ለጤንነት የሚሰጥ በመሆኑ መንግስት በወሰደው እርምጃ ቅሬታ የለኝም ብላለች ።

ኮማንድ ፖስቱ ከከተማ ወደ ከተማ፣ከከተማ ወደ ገጠር የሚደረግ የሰው ዝውውርና በትራንስፖርት፣በመጠጥ ቤቶች በማስዋቢያ ቤቶችና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ ገደብ መጣሉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም