በኮሮናቫይረስ የተያዙ 3 ተጨማሪ ሰዎች ተገኙ

105

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 89 ሰዎች ውስጥ ሦስት ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።

ከዚህ ቀደም በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው የ85 ዓመት ኢትዮጵያዊ አዛውንት አገግመዋል።

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ የተገኙትን ሶስት ሰዎች ጨምሮ በኢትዮጵያ  ውስጥ  በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 38 እንዳደረሰው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ ዛሬ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ሦስቱም ግለሰቦች የውጭ አገሮች ጉዞ ታሪክ ያላቸውና ሁሉም በአዲስ አበባ ይገኛሉ።

''የመጀመሪያው ግለሰብ የ29 ዓመት ወንድ ሲሆን መጋቢት 10 ቀን ከዱባይ የመጣና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ የነበረው ነው'' ብለዋል።

ሁለተኛው የ34 ዓመት ወንድ መጋቢት 23 ከዱባይ የመጣና በማቆያ የነበረና ከበሽታው  ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ የነበረው መሆኑ ታውቋል።

ሶስተኛዋ የ35 ዓመት ሴት በመጋቢት 25 ከስውዲን የመጣችና በማቆያ የነበረች መሆኗን ገልጸዋል።  

ዛሬ ከቫይረሱ ያገገሙትን የ85 አመት አዛውንት  ጨምሮ  በድምሩ  4  ሰዎች  ከቫይረሱ ማገገማቸውን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም አዲስ አበበና ከአዳማ 641 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው  ሲሆን፤ ከዚህም470 ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የገለፁት ሚኒስትሯ ፤የቀሪዎቹ 171 ሰዎች ውጤት እየተጠበቀ መሆኑንም ተናግረዋል ።

ምርምራው የተደረገላቸው ሰዎች የስራቸው ባህሪይ ና በሌሎች ምክንያት ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ናቸው ብለዋል።

የቫይረሱ ምርመራ በአዲስ አበባና በክልሎች የማስፋት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም