ለደቡብ ወሎ 27 የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ

171

ደሴ ፣መጋቢት 26/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዙ 27 የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች በድጋፍ ማግኘቱን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

የመመሪያው ኃላፊ አቶ አንተነህ ደመላሽ እንደገለፁት ከደሴ ሪፈራል ሆስፒታል 10፣ ከቦረና ሳይንት ወግዴ ከለላ ንግድ አክሲዮን ማህበር 15 እና ከኢን ጀንደር ሄልዝ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ደግሞ ሁለት የሙቀት መለኪያዎች በድጋፍ ተገኝቷል ።

በተለይም አካባቢው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በደላሎች ተታልለው በህገ ወጥ መንገድ ወደ አረብ አገር ለመውጣትና ጉዞአቸው ሳይሳካ የሚመለሱ በርካታ ወጣቶች በመኖራቸው በአካባቢው በሽታው ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት አይሎ ቆይቷል ።

ይህንኑ እንቅስቃሴ ለመከላከልም ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አመልክተውዋል።

ከዚህ በፊት በሙቀት መለኪያ ማሽን እጥረት ምክንያት ኮምቦልቻ አየር ማረፊያ ላይ ብቻ ሙቀት የመለካት ስራ ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰው  እጥረቱ በመከላከል ስራው እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልፀዋል።

አሁን ላይ በድጋፍ የተገኙ ማሽኖች የስጋት ቀጠና ተብለው በተለዩ 12 ቦታዎች የሰውነት ሙቀት የመለካት ስራ ለማከናወን ያስችላሉ ።

እንደ ኃላፊው ገለፃ ቃሉ፣ ቦረና፣ ጃማ፣ ደላንታ፣  ውጫሌና ከላላ ሙቀት ከሚለካባቸው ቦታዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተው አገልግሎቱን የሚሰጡ  33 የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ወስደው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አራት ዋና ዋና የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ካምፓስ፣ መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ቱሉ አውሊያና መካነሳላም ካምፓስ እንዲሁም ኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ አስፈላጊው ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው ለለይቶ ማቆያ ተዘጋጅተዋል።

በተጨማሪም በርካታ ባለሃብቶች ሆቴሎቻቸውንና የመስሪያ ቦታዎቻቸውን ሁሉ ለለይቶ ማቆያ በመስጠት አጋርነታቸውን እያሳዩ መሆኑን አመልክተው በገንዘብና በሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች እገዛ እየተደረገ እንደሆነም አመልክተዋል።

የቦረና ሳይንት ወግዴ ከላላ ንግድ አክሲዮን ማህበር ተወካይ አቶ ደመቀ አዳነ በበኩላቸው የኮሮና በሽታ መከላከል ከማንኛውም ተግባር ቅድሚያ ተሰጥቶት መሰራት ያለበት አንገብጋቢ ጉዳይ ንው።

በሽታው የበለፀጉ ሃገራትን ክፉኛ እየተፈታተነ መሆኑን ገልፀው  ይህ በሽታ በታዳጊ ሃገራት ሊያደርስ የሚችለውን የከፋ ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ከወዲሁ መከላከል ይገባል።

ለዚህ ይረዳ ዘንድም ማህበሩ በ110 ሺህ ብር ወጭ የገዛቸውን 15 የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ያስረከበ ሲሆን በቀጣይም መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም