ሳኒታይዘር ነው በማለት ለጤና ጠንቅ የሆነ ኬሚካል ሲሸጡ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

61

አዳማ ፣ መጋቢት 26/2012(ኢዜአ)  በምስራቅ ሸዋ ዞን መተሐራ ከተማ የንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ነው በማለት በጤና ላይ ችግር የሚፈጥር ኬሚካል ሲሸጡ የተገኙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ከአዳማ ከተማ ወደ መተሓራ በመውሰድ  የንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ነው በማለት ለጤና ጠንቅ የሆነ ኬሚካል ሲሸጡ የተገኙ 4 ሰዎች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ገልጸዋል።

የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኦሮ  62888  በሆነ  ዶልፊን  የህዝብ  ማመላለሻ  ተሽከርካሪ  ጭነው  ከአዳማ  በመውሰድ  በመተሀራ ከተማ  እየተዘዋወሩ ሲሸጡ  በህዝብ  ጥቆማ  የህገ ወጥ  ምርቱ ባለቤት ፣ የመኪናው ሾፌርና ሁለት ግብረ አበሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል ።

ግለሰቦቹ  ለፖሊስ በሰጡት ቃል ድርጊቱን እንደፈፀሙ ማመናቸውን ኮማንደር አስቻለው ተናግረዋል ።

ግለሰቦቹ ለገበያ ያቀረቡት የተጭበረበረ ምርት ከላርጎ ሳሙና፣ከሽንት ቤት  ማፅጃ  ዲቶልና  ከሌሎች ኬሚካሎችን በማደባለቅ ያዘጋጁት ሲሆን ሳኒታይዘር የሚል  ፅሑፍ  ለጥፈው ለህብረተሰቡ በመሸጥ ላይ እንዳሉ ነው የተያዙት ።

አራቱምግለሰቦች ጉዳያቸው በምርመራ ላይ መሆኑን የገለጹት ኮማንደሩ  የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ምክንያት በማድረግ በአቋራጭ ለመበልፀግ ያለሙት ስግብግብ ነጋዴዎችና ግለሰቦች በርካታ ወንጀል እየፈፀሙ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ ይህን ተገንዝቦ የተመረተበት ቦታ፣ቀንና የምርት አገልግሎቱ የሚያበቃበት ጊዜ የሌለውን ማንኛውንም አይነት ምርቶች ሲሸጡ ሲመለከት ፈጥኖ ለፖሊስ ጥቆማ በማድረስ የተለመደውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም