የአዳማ ባለሃብቶች ለኮሮና መከላከል ስራ የሚውል 19 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

56

አዳማ፤ መጋቢት 25/2012 (ኢዜአ) የአዳማ ከተማ ባለሃብቶች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተጀመረውን ስራ ለማጠናከር ከ19 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ። 

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የከተማዋ ባለሀብቶች ከህዝብና ከሀገር በላይ ትርፍ የለም በማለት በወረርሽኙ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ርብርብ እያደረጉ ነው ።

በከተማዋ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚያስችል ሀብት ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረት ከ19 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በገንዘብና በአይነት መገኘቱን ተናግረዋል።

በተለይ በሽታው በህዝብ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ባለሃብቶች ከ1 ሺህ በላይ አልጋ የሚይዙ  የተለያዩ ህንፃዎችን መስጠታቸውን ገልጠዋል።

የጎዳና ተዳዳሪዎች በበሽታው እንዳይጎዱ የምግብና የመኝታ አገልግሎት እያቀረብን ነው ያሉት ከንቲባው፤ ከ440 በላይ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናትና ልጆች ወደ ከተማዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሎጅ በማስገባት በዘላቂነት የመኝታና የምግብ አገልግሎት እየተሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ነዋሪዎችና አቅመ ደካሞች ዱቄትና መኮሮኒ በየቀበሌው እየተሰጣቸው ከመሆኑም ባለፈ 2 ሺህ 500 እንጀራና 5 ሺህ ዳቦ በቀን ማረፊያቸው ድረስ እየቀረበላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

ድጋፍ ከሰጡት የከተማዋ ባለሃብቶች መካከል አቶ አብይ አበበ እንደገለጹት ከምናገኘው ገንዘብ በላይ ሀገራችንና ህዝባችንን ከችግር  ለማውጣት  የሚጠበቅብንን  ግዴታ  የመወጣት  ኃላፊነት አለብን ብለዋል ።

"ህዝብ እየሞተ ከዚህ ሆቴል የማገኘው ገቢና ምቾት ከሀገር ጉዳይ  ጋር አላነፃፅርም"  ያሉት ባለሃብቱ ባለ ስምንት ፎቅ ከ300 በላይ አልጋ ያለው ሆቴል ወደ ጊዜያዊ ሆስፒታል ተቀይሮ ለህክምና አገልግሎት እንዲውል መስጠታቸውን ተናግረዋል።

በሽታው ወረርሽኝ ከመሆኑም ባለፈ በየቤታችን የሚገባና የያዝነውን ሀብት ትርጉም የሚያሳጣ ነው ያሉት የገልፍ ሆቴል ባለቤት አቶ ነስረላህ ጣሃ በበኩላቸው  ስርጭቱን   ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ባለ አምስት ፎቅ ሆቴል መስጠታቸውን ገልጸዋል።

የወሰድኩት እርምጃ ሀገር በማዳን ዘመቻ ለመቀላቀል ስለሆነ ከሀገሬና ከወገኔ የሚበልጠብኝ ምንም ነገር ባለመኖሩ 200 አልጋ የመያዝ አቅም ያለውን ህንፃ በፍላጎቴ ሰጥቻለሁ"" ብለዋል ።

በበሽታው ምክንያት የህዝብ እንቅስቃሴ በመገደቡ ኑሮውን በእለት ተዕለት እንቅስቃሴ  የሚደጎመው የህብረተሰብ ክፍል እንዳይቸገር በየቀኑ 5ሺህ ዳቦ ለአንድ ወር እያቀረቡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ኢንጂነር አንዋር ሰይድ የሚባሉ የከተማዋ ነዋሪ ባለሃብት ናቸው።

"ለእኔ ሀብቴ ህዝቤ ነው ያሉት" ባለሃብቱ በቀጣይነት የእለት አቅርቦቱን ወደ 10 ሺህ ዳቦ ለማሳደግና ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎችን ለማድረግ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም