የኦሮሚያ ክልል የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየሰራ ነው

84

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ስርጭት ተስፋፍቶ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል የሕክምና ዘርፉን ከማደራጀት ጀምሮ የተለያዩ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን እየተከናወኑ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል አስታወቀ።

የኮሮናቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ አስንሰቶ ለመከላከል የተቋቋሙ የተለያዩ ኮሚቴዎች የእስካሁኑን አፈፃፀማቸውን በሚመለከት ውይይት አድርገዋል።

በዚሁ መሰረት የመንግስት ውሳኔዎች ተፈጻሚነትን የተመለከተ ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ማህበራዊ ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ቫይረሱን ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉ ውሳኔዎች በጥሩ ሁኔታ እየተፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተሞች የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ላይ የተጣለው ገደብ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሸታ ቤቶች የሚታየው እንቅስቃሴ፣ ስብሰባዎች እንዲቋረጡ እንዲሁም የኃይማኖት ተቋማት ላይ የተጣለው ገደም ከሞላ ጎደል ተፈጻሚ ሆኗል ብለዋል።

በሌላ በኩል በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እነዚህን ውሳኔዎች በተመሳሳይ መልኩ የማፈጸምና የማስፈጽም ችግሮች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንዳሉትም በክልሉ እስካሁን ከ3 ሺህ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል።

ከ2 ሺህ 500  በላይ ነጋዴዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተስጥቷቸዋል።

የንግድ እንቅስቃሴን የሚከታተለው ኮሚቴ እስካሁን በሰራው ስራም ስው ሰራሽ ችግር የሚፈጥሩ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ተደርጓል።

አሁንም ቢሆን ግን የሕብረት ስራ ማህበራትን ጨምሮ አንዳንድ ነጋዴዎች አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያደርጉ መረጃ ደርሶናል እርምጃም እንወስዳለን ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ ኮሚቴውን የሚስተባብሩት አቶ ዳባ ደበሌ እንዳሉትም እስካሁን 46 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዳ ቁሳቁስ ከበጎ ፈቃደኞች ተሰብስቧል።

ከ144 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች በተሳተፉበት በዚህ ሂደት ለ9 ሚሊዮን ሰዎች የፊት ለፊት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት።

በክልሉ የሚገኙ ባለሃብትች እስካሁን ሆቴሎቻቸውን፣ መኪኖቻቸውንና ሌሎች በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ ነገሮች እየገዙ ነውም ብለዋል።

በጤና ኮሚቴም እስካሁን ባለው ሂደት 208 ሰዎች ተለይተው ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ በቫይረሱ የተያዙት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚረዱ የሕክምና መሳሪያዎችን የማሟላት ስራም እየተሰራ መሆኑ ተናግረዋል።

በክልሉ እስካሁን 44 የለይቶ ማቆያ ቦታዎች፣ 107 ሆስፒታሎች፣ 174 ጤና ጣቢያዎች፣ 677 አልጋዎች እና 23 አምቡላንሶች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን ለማዋቅ ተችሏል።

አንዳንድ ፋብሪካዎች ስራ በማቆማቸው በርካታ ዜጎች ስራ አጥ እየሆኑ መምጣታቸውም የሚያሳስብ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በውይይቱ ላይ እንዳሉት የክልሉ ኢኮኖሚ ወደ ቀውስ ሳያመራ በሽታውን ለመከላከል መጣር ያስፈልጋል ብለዋል።

ዋናው ጉዳይ ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ግንዛቤ እንዲጨብጥ በማድረግ ኢኮኖሚው በአግባቡ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በመሆኑም በክልሉ በከተሞች ካሉት የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ውጪ ያሉት ሌሎቹ ስራቸውን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ፋብርካዎች ከምንም በላይ ለጥንቃቄ ትኩርት በመስጠት ስራቸውን እንዲሰሩና አርሶ አደሮችም መደበኛ ስራቸውን እንዲሰሩ ፕሬዚዳንቱ  መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም