ባለፉት ስምንት ወራት ከውጪ ንግድ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ተገኘ

85

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት ከውጪ ንግድ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2012 በጀት አመት 8 ወራት የውጪ ንግድ አፈጻጸም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንዳሉት፤ በስምንት ወር ለማግኘት ከታቀደው 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

አፈጻጸሙ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ170 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወይንም የ10 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ከዋና ዋና የወጪ ምርቶች ውስጥ ትልቁን የገቢ ድርሻ የሚይዘው ቡና ሲሆን ከ460 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝቷል።

ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸርም የ10 በመቶ ጭማሪ ቢያሳይም ከእቅድ አኳያ የሚፈለገውን አፈጻጸም እንዳላስመዘገበ ገልጸዋል።

በቡና አቅራቢዎችና ሰብሳቢዎች የአቅርቦት ዋጋ መጨመር እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአሰራር ስርአት አለመሻሻል አፈጻጸሙ ዝቅ እንዲል ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ አንስተዋል።

በሁለተኛነት በገቢ አፈጻጸም የተሻለ ድርሻ ያለው የአበባ ምርት ሲሆን ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝቷል።

በስምንት ወራቱ ከቅባት እህሎች የተገኘው ገቢ 188 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም የሰሊጥ ምርት በብዛት የምትቀበለው አገር ቻይና ውስጥ በተፈጠረው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አፈጻጸሙ ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል።

''ጨርቃጨርቅና አልባሳትም የተሻለ አፈጻጸም አሳይተዋል'' ተብሏል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የጥራጥሬ ሰብሎች ወጪ ንግድ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 22 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

በተመሳሳይ ከቁም እንስሳት ዘርፍ 40 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ቢገኝም ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር 20 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል።

በ2012 በጀት አመት ከውጭ ንግድ 3 ነጥብ 73 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በአለም ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ተጽእኖ በቋቋም እቅዱን ለማሳካት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የግብርና ምርት ላይ እሴት ጨምሮ አለመላክና ዘርፉን በምርምር አለመደገፍ፣ በአምራች ዘርፉ ላይ የሚስተዋለው የሃይል መቆራረጥ፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት፣ ህገወጥ ንግድን በበቂ መጠን አለመቆጣጠር ትኩረት የሚሹ ችግሮች መሆናቸው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም