የደሴ ጊዜያዊ መጅሊስ በምፅዋት ለሚተዳደሩ አቅመ ደካሞች ድጋፍ አደረገ

128

ደሴ/ ወልዲያ ኢዜአ 25/7/2012 በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቤተ እምነቶች በመዘጋታቸው በምፅዋት ይተዳደሩ የነበሩ ወገኖች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ 20 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ጊዜያዊ መጅሊስ አስታወቀ፤' 

በደሴ ከተማ የጊዜያዊ መጅሊስ ፕሬዝዳንት ሼህ እንድሪስ በሺር ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በኮሮና ቫይረስ ስጋት በመስጊድ በሮች ላይ ህዝበ ሙስሊሙ በሚሰጣቸው ምፅዋት ይተዳደሩ የነበሩ አቅመ ደካማ ወገኖች መስጊዶች በመዘጋታቸው ለችግር ተጋልጠዋል ።

ጊዜያዊ መጅልሱም ይህንኑ ችግር ታሳቢ በማድረግ 20 ሚሊየን ብር መድቦ አቅመ ደካሞችን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል ።

በዚህ መሰረት ለ500 አቅመ ደካሞች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችል የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲሁም፣ 100 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ 15 ኩንታል ሩዝና ሌሎች የምግብ እህሎችን እንዲሰጣቸው ተደርጓል ።

መስጊዶች በተዘጉበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ድጋፉ መደረጉ በልመና የሚተዳደሩ ወገኖችን ከሚደርስባቸው ሰቆቃ እንደሚታደግ ሼህ እድሪስ ገልፀዋል ።

ድጋፍ ከተደረገላቸው አቅመ ደካማ ወገኖች መካከል የአካል ጉዳተኛ የሆኑት አቶ አህመድ ሙሳ "የአካል ጉዳተኛና የሚረዳኝ ዘመድ የሌለኝ በመሆኑ በመስጊድ በሮች በመለመን ምዕመኑ በሚሰጠኝ የምፅዋት ገንዘብ ህይወቴን ስመራ ቆይቻለሁ"።

ይሁን እንጂ ከኮሮና መከሰት ጋር ተያይዞ መስጊዶች ሲዘጉ "ለምኜ የማገኘው የእለት ምግብ አጣለሁ የሚል ስጋት ቢያድርብኝም መጅልሱ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ስላደረገልኝ ከበሽታው እንድጠበቅና ቀለብ እንዳገኝ አግዞኛል " የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ድሃው ህብረተሰብ እንደይጎዳና የኮሮና በሽታን ለመከላከል 100 ሚሊየን ብር በማሰባሰብ ላይ መሆኑን ገልጾ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሰራ መሆኑን ገልጿል ።

ጊዜያዊ መጅሊሱ በራሱ ተነሳሽነት ገንዘብ መደቦ በልመና የሚኖሩትን መደገፉ ለሌሎችም የሃይማኖት ተቋማት አርአያ ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የከተማ አስተዳድሩ ጠይቋል ።

በተያያዘ ዜና በሰሜን ወሎ ዞን የኮሮና በሽታ ወደ ገጠሩ አካባቢ እንዳይስፋፋ የሚያስችል ስልት ቀይሶ እየሰራ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደ ትንሳኤ መኮነን ገልጸዋል።

በገጠሩ አካባቢ የሚገኘው ህብረተሰብ ንጽህናውን እንዲጠብቅ፣ አካላዊ ርቀትን ጠብቆ እንዲጓዝና ሌሎች የኮሮና በሽታ መከላከያ መንገዶችን እንዲፈጽም ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

የዞኑ ባለሃብቶችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚውል ከ6.7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መገኘቱም ተገልጻል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም