የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ አደረገ

88

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ የንጽህና መጠበቂያ ግብአቶችን ለተፈናቃዮች ድጋፍ አደረገ። ጉባኤው የንፅህና መጠበቂያዎቹን ዛሬ የለገሰው ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተፈናቅለው በሰበታ መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ነው።

ድጋፉም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችል 800 ሊትር አልኮሆልና 800 ሊትር ፈሳሽ ሳሙና መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ የንጽህና መጠበቂያዎቹን ለሰበታ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ አስረክበዋል ።

የኮሮናቫይረስ ዓለምን እያሰጋ ያለ ወረርሽኝ ስለሆነ ሁሉም ሰው ይህንን ቫይረስ ለመግታት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በማሰብ ድጋፉ መደረጉን ተናግረዋል።

ድጋፉ በኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና በ'ኖርዌጂያን ኤይድ ሰርቪስ' ትብብር የተደረገ መሆኑንም ቀሲስ ታጋይ ገልፀዋል።

ድጋፉ በዋናነት በመጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች የሚውል መሆኑን አመልክተዋል።

ድጋፉ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቀሲስ ታጋይ ተናግረዋል።

በርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የሰበታ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኩል ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

አቶ ብርሃኑ የሃይማኖት አባቶች የግብአት ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በየእምነታቸው የሚያደርጉትን ጸሎት እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በሚደርስበት ጊዜ ለህብረተሰቡ እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን በስነ-ስርአቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም