ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃው ይቀጥላል

93

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2012 (ኢዜአ) ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ምርት በሚደብቁ የንግድ ተቋማት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ። 

ቢሮው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መከሰት ተከትሎ በገበያው የተፈጠረውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከመድኃኒት አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

አንዳንድ ነጋዴዎች ወቅታዊው ሁኔታውን እንደ ትርፍ ማግበስበሻ ሲጠቀሙበት መስተዋሉ በመድረኩ ተገልጿል።

ምርት በመደበቅና ዋጋ በመጨመር የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር ምክንያት የሆኑበት ሁኔታም እንዲሁ።

የመድረኩ ዓላማ የመድኃኒት አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮች ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻልና ለተስተዋሉ ችግሮች በጋራ መፍትሄ ለማምጣት መሆኑ ታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ ዩሱፍ ከውይይቱ በኋላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የነጋዴው ዋና ችግር የንግድ አሰራር ጉድለት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ምርት መገደብ፣ መደበቅ፣ ማከማቸት፣ ለተወሰኑ ነጋዴዎች ብቻ ምርት በማቅረብ የግብይት ሰንሰለቱን የማራዘም አሰራር ጉድለቶች መስተዋላቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በደላላ በኩል መሸጥ፣ በችርቻሮ ፈቃድ የጅምላ ንግድ ማካሄድና በማይታወቅ አካባቢ ምርት በማከማቸት የምርት እጥረት እንዳለ በማስመሰል ዋጋ መጨመር የታዩ ችግሮች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለአብነትም ሳኒታይዘር ባለ 250 ሚሊ ሌትር በ87 ብር ይሸጥ የነበረውን በ185 ብር፣ አልኮል በሊትር 40 ብር የነበረውን 125 ብር እንዲሁም የእጅ ጓንት 100 ፍሬ 85 ብር የነበረውን እስከ 129 ብር ድረስ በመሸጥ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

ቢሮው በከተማዋ ባሉ 30 ሺህ የንግድ ተቋማት ላይ በቅርቡ ባደረገው ምርመራ ምርት በደበቁናና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል በተባሉ 2 ሺህ 70 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን አቶ አብዱልፈታህ ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስ ከረዥም ጊዜ አንጻር በምርትና አቅርቦት ሂደት ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር ቢችልም በአሁኑ ወቅት የምርት እጥረት ሳይኖር ሰው ሰራሽ በሆነ ምክንያት በአቅርቦት ላይ ችግር መስተዋሉን አመላክተዋል።

"ከመድኃኒት አምራቾች፣ አስመጪዎች እና አከፋፋዮች በዚህ ወሳኝ ወቅት የሚጠበቀው ከህዝብ ጎን መቆም ቢችሉ በነፃ ማቅረብና በቅናሽ ዋጋ መሸጥ፤ ካልሆነ ደግሞ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አለማድረግ ነው" ብለዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ይሄንን በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና ለህዝቡ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩም ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም