የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

107

መጋቢት 25/2012 ኢዜአ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ሃይለየሱስ በቀለ ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በመገኘት የተለገሰውን ገንዘብ አስረክበዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉትም ከተለገሰው 5 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች እያንዳንዳቸው የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመለገስ ቃል ገብተዋል።

የአመራሩ ግንባር ቀደም መሆን ለሌሎቹ የተቋሙ ሰራተኞችም የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ ባንኩ ላደረገው ልገሳ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዚህ ሳምንት በተካሄደው የቦንድ ሽያጭ እስካሁን 7 ሚሊዮን 302 ሺህ ብር መሰብሰቡንም አስታውሰዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በኢትዮጵያዊያን ሃብትና ጉልበት ለመገንባት የዛሬ 9 ዓመት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት አሁናዊ አፈፃፀሙም ከ72 ነጥብ 4 በመቶ በላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም