የደብረ ብርሃን፣ አርባ ምንጭና አሶሳ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን አስመረቁ

58
ደብረብርሃን /አርባ ምንጭ/አሶሳ ሰኔ 24/2010 ደብረ ብርሃን፣ አርባ ምንጭና አሶሳ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠኗቸውን 5ሺህ 456 ተማሪዎች አስመረቁ ። የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አሰልጥኖ ዛሬ ካስመረቃቸው 3 ሺህ 269 ምሩቃን መካከል 1 ሺህ 266ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ በምረቃ ስነስርአቱ ላይ እንደተገለጸው ከምሩቃን ተማሪዎች መካከል 3 ሺህ 121 በመጀመሪያ ዲግሪ የሰለጠኑ ሲሆን፣ 148ቱ በሁለተኛ ዲግሪ መሰልጠናቸው ታውቋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተፈራ ምሩቃን በተቋሙ ያገኙትን ዕውቀት ወደ ትግባር ቀይረው አገሪቷን ከድህነትና ከኋላቀረነት ሊያላቅቁ እንደሚገባ በምረቃው ላይ ተናግረዋል። ራሳቸውን ከተለያዩ ሱሶችና ሌብነትም በመጠበቅ በአገሪቱ ኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት አሻራቸውን ማስቀመጥ እንዳለባቸው ገልጸው ህዝቡን  በቅንነት፣ በታማኝና በታታሪነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባልና የዕለቱ የክብር እንግዳ ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማሪያም በበኩላቸው የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ምሩቃን በሚሰማሩበት የሥራ መስክ ሁሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ እውቀት በተለያየ ጊዜ እንደሚገኝ ሁሉ ሲተው ስለሚረሳ አሁን ያገኙትን እውቀት እያዳበሩ መሄድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በአጠቃላይ ውጤት 3 ነጥብ 98 በማምጣት የሁለት ዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ተመራቂ እታገኝ ብዙነህ በሰጠችው አስተያየት ለውጤቷ መሳካት ከግል ጥረት በተጨማሪ የምስጉን መምህራንና የቤተሰቧ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጻለች፡፡ "ወደ ስራው አለም ስገባም ከተለያዩ ሱሶች ራሴን ጠብቄ በተማርኩበት የትምህርት ዘርፍ ለኢትዮጵያ ልማትና እድገት የድርሻዬ እወጣለሁ" ብላለች፡፡ ሌላዋ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ 3 ነጥብ 81 በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ጫልቱ ታከለ በበኩሏ በሰለጠነቸበት ሙያ ሕብረተሰቡን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቷን ተናግራለች፡፡ በተለይም በህክምና ስህተት የሚሞቱ ህሙማንን ሕይወት ለመታደግ  ሙያዊ ግዴታዋን በአግባቡ ለመወጣት ሌት ተቀን እንደምትሰራ ነው የገለጸችው፡፡ በተመሳሳይ ዜና  በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሳውላ ካምፓስ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 130 ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ አስመርቋል፡፡ በምረቃው ላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ እንዳሉት መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ ባደረገው እንቅስቃሴ የሳውላ ካምፓስ በ2008 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡ እንደ ዶክተር ዳምጠው ገለጻ ዛሬ ለምርቃ ከበቁት 130 ተማሪዎች መካከል 64ቱ ሴቶች ናቸው። የዕለቱ ምሩቃን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት ጠንክረው በመስራት አርአያ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በምረቃ ሥነስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኢታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ የተማረ የሰው ኃይል ለአገራዊ ልማት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። "በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሳውላ ካምፓስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍሬ መብቃቱ ከፍተኛ ትምህርት ዕድል ማግኘት ላልቻሉ ኢትዮጵያዊያን ምላሽ የሰጠ ነው" ብለዋል ፡፡ በተያያዘ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በስምንት የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 57 ተማሪዎችን በዛሬው እለት አስመርቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአምስተኛ ዙር ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 27ቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸው ናቸው፡፡ በምረቃት ስነስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አምሳሉ በዲሞ ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ማህበረሰባቸው ለመለወጥ እንዲያውሉት አሳስበዋል፡፡ ተመራቂዎች በአገሪቱ እየተፈጠረ ባለው የለውጥ ሂደት የራሳቸውን አሻራ ለማበርከት ተግተው እንዲሰሩም አስገንዝበዋል፡፡ ከዕለቱ ምሩቃን መካከል በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁት አቶ አራጋው አደም "ዩኒቨርሲቲው በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ማሰልጠን በመጀመሩ የትምህርት እድሉ በቅርበት አግኝቺያለሁ" ብለዋል፡፡ አገሪቱ አዲስ የለውጥ ተስፋ የሰነቀችበት ወቅት እንደመሆኑ በተመረቁበት የትምህርት መስክ ባገኙበት እውቀት የድርሻቸውን ለማበርከት ለውጡን ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡ የማዕረግ ተመራቂ የሆነችው አክሱማይት ገብረፃድቃን በበኩሏ ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀምና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተባብራ በመስራቷ ውጤታማ መሆኗን ተናገራለች፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች ባህልና አኗኗር ያላት ግንዛቤ ማደጉን አስታውቃለች፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም