በኮምቦልቻና ድሬዳዋ የኬሚካል ርጭት ተካሔደ

67

ደሴ /ድሬዳዋ ኢዜአ መጋቢት 25/2012 የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በኮምቦልቻና በድሬዳዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ  የፀረ ተህዋስያን ኬሚካል ርጭት መካሔዱን የከተሞቹ የስራ ኃላፊዎች ገለፁ ።
የኮምቦልቻ ጤና ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አበራ ለኢዜአ እድገለጹት በከተማዋ የኮሮና ቫይረስ እንዳይከሰት ከተከሰተም ፈጥኖ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።

በዛሬው እለትም የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ፀረ ተህዋስያን ኬሚካል ተረጭቷል።

በርጭቱ 57 ሺህ ሊትር ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉንም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳይፈጠር በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑንም ነው ኃላፊው አያይዘው የገለጹት።

በተመሳሳይ ሁኔታ በድሬዳዋ ከተማ ዋናዋና መንገዶች ላይም ዛሬ ጥዋት የኬሚካል ርጭት ተካሔዷል ።

የኬሚካል ርጭቱ የተካሔደው በከተማው ሥራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት ፣ በድሬዳዋ ጤና ቢሮና ፖሊስ ኮሚሽን ቅንጅት ነው ።

የፀረ- ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭቱ በዋና ዋና የአስፋልት መንገዶችና ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ የተካሄደ ሲሆን በሰፈሮችና በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይም ይቀጥላል ተብሏል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ. ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ፤ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

እነዚህ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ በጤና ሚኒስቴር በኩል በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ የመከላከያ መመሪያዎችን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም