የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሀገራት እርምጃ

80

በገዛኸኝ ደገፉ (ኢዜአ)

በሳይንሳዊ መጠሪያው COVID- 19 በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ በሀገረ ቻይና ያለፈው ታህሳስ ወር ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ መላውን ዓለም እያስጨነቀ፤ ከቀን ወደቀን የመስፋፋት ፍጥነቱን እና አድማሱን እያሰፋ ዛሬ ላይ ከ 1ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ ለሞት የዳረጋቸው  ሰዎች ደግሞ ከ53 ሺህ በላይ ደርሷል። ይህ ወረርሽኝ በርካታ የዓለም አገራት በተለይ በስልጣኔ ማማ ላይ ያሉ ከወትሮው በተለየ መልኩ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ከተሞቻቸውን ቆልፈው ከቤት ውጪ የሚንቀሳቀስ ከተገኘ ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቀው በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። 

ወረርሽኙ የተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ውሃን ከተማ ለሁለት ወራት ያህል እንቅስቃሴ ሳይታይባት ረጭ ብላ አሳልፋለች። የአገሬው መንግስት ባደረገው ርብርብ ስርጭቱን ለመቆጣጠር በመቻላቸው በቅርቡ በመጠኑም ቢሆን እንቅስቃሴ እየታየባት ሲሆን የግዛቱ አስተዳዳሪዎችም ወደ ሁቤይ መግባትና መውጣት እንደሚቻል መፍቀዳቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሁሉም የቻይና ግዛቶች ተንሰራፍቶ የከረመው ድብታ ቀስ በቀስ እየለቀቀ የተለመደው አይነት ህይወት እንዲቀጥል ባለስልጣናቱ ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑ የሚናገሩት የአለም ሚዲያዎች በሽታው የጀመረባት ዉሃን ከተማ ግን አሁንም የህመምተኛ ገጽታ ላይ ነች ብለዋል።

የአለም ጤና ድርጅት በቻይና ያለውን የወረርሽኙን አደጋና አጠቃላይ የጤና ሁኔታዎች በቅርበት እየተከታተለ ምንም አስጊ ነገር እንደሌለና ሱቆች እንዲከፈቱ ቀዝቅዘው የነበሩ የፋብሪካ ማሽኖች እንዲሞቁ፣ ተሽከርካሪዎች ወደ ጎዳና እንዲወጡ፣ ቻይናውያን ወደ ቀደመ ስራቸውና ህይወታቸው እንዲመለሱ ሃሳብ ቢያቀርብም የቻይና ዜጎች አሁንም ከፍርሃቱ የታሰበውን ያህል ሊላቀቁ አልቻሉም ነው የተባለው። እንደ ቻይና ዴይሊ ዘገባ አሁን ላይ አዳዲስ የበሽታው ተጠቂዎች ከውጭ ሃገራት ወደ ቻይና እየገቡ ቢሆንም ከአካባቢዎቹ አስተዳደሮች ቁጥጥር ውጭ እንደማይሆን ነው የተነገረው።

የቻይና ጎረቤት የሆነችው ህንድ የቫይረሱ መስፋፋት የሃገሪቱን ባለስልጣናትና የህክምና ባለሙያዎች እንቅልፍ ማሳጣት ከጀመረ የሰነበተ ሲሆን ከቀናት በፊት 1.3 ቢሊየን የሚሆኑት ዜጎቻቸውን ቤታቸው ውስጥ እንዲሰነብቱ ከብርቱ ቅጣትና ጠንካራ ቁጥጥር ጋር ማውጣቷን የአለም ሚዲያዎች ሲቀባበሉት ቆይተዋል። ድህነት እጅጉን በከፋባቸው የህንድ ግዛቶች ዜጎች ከቤት ሳይወጡ እንዲቆዩ መደረጉ ደሆችን ለሌሎች በሽታዎች ማጋለጥ መሆኑን አንዳንድ ራሳቸውን የመብት ተሟጋች አድርገው የሚያቀርቡ ግለሰቦች ቢናገሩም መንግስት አቅም በሚፈቅደው መጠን የእለት ጉርሳቸውን እያከፋፈለ ስለመሆኑና ይሄንን ጊዜ ተባብሮ ማሳለፍ የመብት ተማጋቾቹም ተግባር ጭምር መሆን እንዳለበት በርካቶች ይስማማሉ።

በአሜሪካ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል እንቅስቃሴዎችን ከመገደብ አንስቶ የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ የተያዘው ሰው ቁጥር ከ245,373 በላይ መሆኑንና ህይወቱን ያጣው ሰው ደግሞ  ከ6,090 በላይ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አሜሪካ በቫይረሱ በተያዘ ሰው ብዛት ከዓለማችን የጀመሪያውን ደረጃ የምትይዝ ሲሆን በቀጣይም የስርጭት አድማሱ ሊሰፋ እንደሚችል የሀገሪቱ ባለስልጣናት እያስጠነቀቁ ይገኛሉ። 

ወደ ኢራን መለስ ስንል ደግሞ በአንድ በኩል በአሜሪካ ማእቀብ ጫና የበረታባት ሲሆን በሌላ በኩል በCOVID- 19 ወረርሽኝ አዲስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ስለመምጣቱ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢራናውያን ያድናሉ ያሏቸውን መድሃኒቶች በዘፈቀደ በመሞከር ላይ መሆናቸው የሳይንስ ሜጋዚን ድረገጽ በስፋት የዘገበው ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ባለው መረጃ ወደ 3ሺህ 160 የሚጠጋ ዜጎቿን የቀበረችው ኢራን ያለ ሃኪም ትእዛዝ የሚወስዷቸው መድሃኒቶች በህክምና ማእከላቱና ባለሙያዎቹ ላይ ስራ በመጨመር ሌላ ራስ ምታት እንደሆኑባት አመልክቶ ነገሮች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ ኢራን ከ100 ሺህ በላይ ዜጎቿን በሞት ልትነጠቅ እንደምትችል ስጋቱን አስቀምጧል።

ወረርሽኙ በከፋ ሁኔታ ከመታቸው የአውሮፓ ሃገራት መካከል ጣሊያንና ስፔን የሚጠቀሱ ሲሆን በእነዚህ ሀገራት ወረርሽኙ ሲከሰት እምብዛም ትኩረት ሳይሰጡት ውስጥ ውስጡን ከተሰራጨ በኋላ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቢጥሩም ስርጭቱ ቀይ መስመሩን በማለፉ በየእለቱ ከፍተኛ የሞት ምጣኔ የሚያስመዘግቡ አገራት ሆነዋል። በአሁኑ ወቅት በጣሊያንም ሆነ ስፔን እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ የሚገድቡ እርምጃዎች የተወሰዱ ቢሆንም እያስከተለ ያለው ቀውስ ግን እጅግ የከፋ ሆኗል።

በእንግሊዝ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ 2 ሺህ 921 ሲሆን መንግስት በወቅቱ መወሰድ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎችና ግልጽ የሆነ መመሪያ አልሰጠም ሲሉ ዜጎች እየተቹ ይገኛሉ። በአሁነ ወቅት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን እራሳቸውን ለይተው ከሚገኙት ቦታ ሆነው መመሪያ ሲያስተላልፉ ነበር።

የCOVID- 19 ወረርሽኝ በአፍሪካ መከሰቱ የተገለጸው ዘግየት ብሎ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከ46 አገራት በላይ በመስፋፋት ላይ ይገኛል። አገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ደቡብ አፍሪካ ኬንያ፣ ጋና፣ ሩዋንዳ፣ ጋቦን የመሳሰሉት ወረርሽኙ የተከሰተባቸው ሲሆን ስርጭቱን ለመከላከል እየወሰዷቸው ከሚገኙት እርምጃዎች መካከል ሁሉንም አይነት በረራዎችን ማሰቆም፣ ድንበር መዝጋት፣ ተጨማሪ የምርመራና ማቆያ ማእከላትን ማዘጋጀት፣ እንቅስቃሴዎችን መገደብ ይገኝበታል። እነዚህ እርምጃዎች የቫይረሱን ስርጭት ከመግታት አንፃር የሚኖራቸው ሚና ምን ያህል እንደሚሆን በቀጣይ የሚታይ ሆኖ ወረርሽኙ እያስከተለ ካለው ቀውስ አኳያ ሲታይ ግን የመንግስታቱ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሁም የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሚሻ ግልጽ ነው።

የብሩክሊን ተቋም ሰነድን ዋቢ ያደረገው የፎሬን ፖሊሲ ጽሁፍ እንደሚያመለክተው ይሄ ክስተት አፍሪካን ለተጨማሪ 10.6 ቢሊየን ዶላር የጤና በጀት ወጪ በመዳረግ አመታዊ እድገቷን በ1.4 በመቶ የሚጎትተው መሆኑን በመጥቀስ የበሽታው መስፋፋት ሊገታ ካልቻለ ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገራት እርስበርስ የሚኖራቸውን የንግድ ልውውጥ በመጉዳት የከፋ ቀውስ ላይ እንደሚጥላቸው ስጋቱን አስቀምጧል። ይህ ወረርሽኝ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው አገራትን በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተነ መሆኑ ሲታይ በደሃ አገሮች ላይ ጫናው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

በኢትዮዽያም ኮቪድ-19 መከሰቱን ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ ስርጭቱን ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 29 የደረሰ ሲሆን ት/ቤቶች ዝግ ሆነው እንዲቆዩ፣ የመንግስት ሰራተኞችም ከቤታቸው ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ፣ በርከታ የአየር በረራ ለግዜ እንዲቋረጥ፤  ከውጭ አገራት ወደ አዲስ አበባ የሚገቡት ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ፣ የገበያ ስፍራዎችና የሃይማኖት ተቋማት ማህበራዊ ርቀትን እንዲጠብቁ፣ የእምነት ተከታዮች በቤታቸው ሆነው እንዲጸልዩም ና በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የከተማ ውስጥ ና ከክልል ወደ ክልል የሚደረግ አገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት  እንዳይንቀሳቀሱ ውሳኔ ተላልፎ ተግባራዊ መደረግ ተጀምሯል።   

የተለያዩ አገራት በተለይም በኢኮኖሚ የዳበሩት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ወረርሽኙን ለመከላከል ንክኪ እንዳይኖር ማድረግ ዋነኛው እርምጃ ሲሆን ለዚህም በቤት ውስጥ መቆየት “Stay home” በሚል መሪ መልእክት ጥብቅ ቁጥጥር እያደረጉ ይገኛሉ። በእኛ አገር ሁኔታ ሲታይ እስካሁን መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች የሚበረታቱ ቢሆንም ከተለመደው አኗኗራችን አንፃር ርቀትን በመጠበቅ በኩል ምንም የተለወጠ ነገር እየታየ አይደለም። በመሆኑም ነገ ተጨማሪ ዋጋ የሚያስከፍለንና የከፋ ነገር ውስጥ እንዳንገባ መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ ከሌላው ዓለም ትምህርት በመውሰድ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት ይጠበቅብናል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም