19 የተለያዩ ድርጅቶች ለኮሮናቫይረስ መከላከያ 47 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

68

ኢዜአ፤ መጋቢት 24/2012(ኢዜአ) 19 የተለያዩ ድርጅቶች ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚሆን የ47 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረከቡ።

ድጋፉን ያደረጉት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኤለክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮፖሬሽን፣ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ እና ወጋገን ባንክ እያንዳንዳቸው የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

ዳሽን ቢራ፣ ቡና ባንክ እና  ላየን ኢንተርናሽናል ትረዲንግ ደግሞ እያንዳንዳቸው ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

በተጨማሪም ጊፍት ሪልእስቴት፣ ቫርነሮ ኮንስትራክሽን፣ ሐበሻ ቢራ፣ ሲ ኤንድ ኢ ወንድማማቾች የብረት ፋብሪካ ብርሃን ኢንሹራንስ፣ ፋንቱ ሱፐር ማርኬት፡ ገነት ሆቴል፣ ድሬ ቴራ እያንዳንዳቸው የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የብሄራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው አባል አምባሳደር ምስጋና አረጋ በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ በመገኘት ስለተደረገው ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኮሚቴው ለሎች ድርጅቶችም ቫይረሱን ለመከላከል የቀረበውን ጥሪ ተቀብለው የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ በማቅረብ፤ ድጋፍ  ያደረጉት ድርጅቶችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ድርጅቶቹ ከድጋፍ በተጨማሪ ተገልጋይ ደንበኞቻቸው እና ሰራተኞቻቸው በጤና ሚኒስቴር የሚተላለፉ የመከላከያ መንገዶችን እንዲተገብሩ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው እስካሁን በሶስት ዙር 129 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም