የኢኮኖሚና አገልግሎት ዘርፎች ቫይረሱን በመከላከል ስራቸውን ተረጋግተው እንዲያከናውኑ ተጠየቀ

68

መቀሌ መጋቢ 24/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከተጠቀሱ ክልከላዎች በስተቀር የኢኮኖሚና አገልግሎት ዘርፎች በተረጋጋ መንገድ ማስቀጠል እንደሚገባ ጊዜያዊ የክልሉ ኮማንድ ፖስት ገለጸ።

በኮማንድ ፖስቱ  የኢኮኖሚ ንኡስ ኮሚቴ አስተባባር ዶክተር መብራህቱ መለስ ዛሬ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን ጤና ጉዳይ ከሁሉም ነገር በማስቀደም ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት  ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ባላቸው ጉዳዮች ላይ እገዳ ጥሏል።

 ክልከላ ከተጣለባቸው ጉዳዮች ውጭ ያሉ የማኑፋክቸሪንግና አገልግሎት ሰጪ የግልና የመንግስት  ተቋማት መደበኛ ስራቸው መቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል።

መንግስት አገልግሎቶችን ማስቀጠል በሚገባቸው ተቋማት ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እንደሚጀምር ተናግረዋል።

በሽታውን ለመከላከል በተወሰደው የክልከላ እርምጃ  በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ ለመቀነስ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ።

በተለይም በአምራች ዘርፎች የሚገኙ ሰራተኞችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ መደበኛ ስራቸውን መቀጠል ይገባል ብለዋል።

በተለይም መንግስት ለግብርና ስራዎች የሚያስፈልጉ ግብአቶች እንደሚያቀርብ ዶክተር መብራህቱ ተናግረዋል።

ወቅቱ  የእርሻ ዝግጅት የሚደረግበት  በመሆኑ አርሶ አደሮች በሽታው ለመከላከል ሲባል የተጣሉ ክልከላዎችን በማክበር መደበኛ ስራቸው እንዲያከናውኑ ኮማንድ ፖስቱ ጥሪ አቅርበዋል።

መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ፍትሃዊ ስርጭቱን ጠብቆ  ለህብረተሰቡ እንዲደርስ መንግስት እየተከታተለው መሆኑንም ገልጸዋል።

"ህብረተሰቡ በረሃብ እናልቃለን " በሚል የአሉባልታ ወሬ በመደናገጥ መጨናነቅና ከአቅም በላይ ምርት ማከማቸት ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

ክልከላው  የፋይናንስ ተቋማትና የምግብ እህል  አቅራቢዎችና ቸርቻሪዎች የማይመለከት መሆኑን በመገንዘብ በተረጋጋ ሁኔታ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።

ህብረተሰቡ ለጊዜው የማይጠቀምበት  ገንዘብ ከባንኮችና ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የማውጣት ዝንባሌም መታረም አለበት ብለዋል።

የተቆጠበ ገንዘብ ከባንኮች ማሸሽ ለክልሉ ኢንቨስትመንትና የገንዘብ ዝውውር የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ጧሪ ለሌላቸው አረጋውያን ፣ ተፈናቃዮች ፣ አካል ጉዳተኞችንና የጎደና ተዳዳሪዎች  በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንዲያገኙ የማስተባበር ስራ እየቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።

በሸቀጦች ላይ አላስፈላጊ  የዋጋ ጭማሪ የሚያሳዩ ነጋዴዎች መንግስት  የህግ እርምጃ እየወሰደ ነው ያሉት ዶክተር መብራህቱ እስከ አሁን የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 500 የንግድ ተቋማት አንዲታሸጉ መደረጉን አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም